ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ነው ሲል አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ ተናገረ።
ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና በሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ መካከል ከትላንት በስትያ ተፈርሟል።
በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን፤ ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንደምታገኝ ተመላክቷል።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ፤ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ ነው ብሏል።
የመግባቢያ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ ያላትን ጂኦ ፖለቲካል አቅም ጥቅም ላይ ለማዋልና የባህር በር ካለመኖር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለማስቀረት እንደሚያስችልም ተናግሯል።
በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ ማግኘቷም የአገሪቱን ሰላም እንዲሁም የቀጣናውን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እድል እንደሚሰጥ ጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ ወደብን በማልማት ዓለም አቀፍ ንግድን ለማሳለጥ በምታከናውነው ተግባራት ሶማሌላንድም የራሷን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችላትም ተናግሯል።
በኢትዮጵያ መንግሥትና ሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሥምምነት በተለይም በቀጣናው ትስስር ለመፍጠር ለአካባቢው አገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ብሏል።
ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌላንድና ጂቡቲ በምሥራቅ አፍሪካ አዲስ የትብብር ኮሪደር በመፍጠር በቀጣናው የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እድል እንደሚፈጥርም ገልጿል።