በታሪካዊቷ ላሊበላ የገና በዓል ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በታሪካዊቷ ላሊበላ የገና በዓል ላይ ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው
ወልዲያ ፤ ታህሳስ 24 /2016 (ኢዜአ)፡- በታሪካዊቷ ላሊበላ የገና በዓልን ለማክበር የሚመጡ የሃገር ውስጥና የውጪ ሃገራት እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የላልይበላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማው አስተዳደር ከንቲባ አቶ ወንድምነው ወዳጅ እንደገለጹት፤ መጪውን የገና በዓል በላሊበላ በድምቀት ለማክበርና ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል።
ለዚህም በማህበርና በቡድን ለሚመጡ ምእመናን የድንኳን መትከያ የወልና የግል ቦታዎች ፀድተው የእንግዶቹ መምጣት እየተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህም ሌላ በከተማው ከ10 በላይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ቦኖዎችና የንጽህና መጠበቂያ መገልገያዎችን ለምዕመኑ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
እንግዶችን አሳፍረው ለሚመጡ ተሽከርካሪዎችም የማቆሚያ ቦታ እንዳይቸገሩ በመናኸሪያና በስታዲየሙ እንዲገለገሉ መመቻቸቱን አስታውቀዋል።
እንዲሁም በከተማው 1 ነጥብ 8 ሎ ሜትር መንገድ ጠረጋ በማከናወን ለእንግዶቹ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ከባህር ዳርና ጎንደር ወደ ላሊበላ የአየር በረራ እንዲፈቀድም ተደርጓል ብለዋል።
በከተማው የሚገኙ 30 ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ሆነው እየጠበቁ ሲሆን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ ያሉ 19 እድሮች በከተማው አራት በሮች ለሚገቡና ለሚወጡ ምዕመኖች ለማስተናገድ እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።
በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ሊከሰት የሚችልን የስርቆት ወንጀል ከመከላከል ባለፈ ወንጀሎች ቢኖሩ ከበዓሉ ዋዜማ እስከ ማግስቱ ድረስ የሚዘልቅ ጊዜያዊ ችሎት ተቋቁሟል ብለዋል።
የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አስተዳዳሪ አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ መጪውን የልደት በዓል ለማክበር እየተዘጋጀን ነው ብለዋል።
በዓሉን ለመታደም ከሃገር ውስጥና ከውጭ አገራት የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ተቀብሎ ለማስተናገድ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የ"ፍስክ" በዓሉ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ 28 የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው፣ ሁሉም የሚደመምበት የቤዛኩሉ ስነ-ስርዓት ደግሞ ታህሳስ 29 የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል።
ላሊበላ 19 እድሮች ህብረት ሰብሳቢ አቶ ደባሽ ጌታመሳይ ፤ በሁሉም የከተማችን በሮች ለሚመጡ እንግዶች ተገቢ የማረፊያ ቦታ እንዲያገኙ ለማስተናገድ እድሮች ዝግጁ ነን ብለዋል።
''በበዓሉ እርድ አዘጋጅተን በቆየ እንግዳ አቀባበልና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ለማስተናገድ ተዘጋጀተናል'' ብለዋል።
በአማራ ክልል ገና በላሊበላ እና ጥምቀት በጎንደር በየዓመቱ በድምቀት እንደሚከበር ተመልክቷል።