የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲና የተደማጭነት አቅም ማሳያ ነው -የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲና የተደማጭነት አቅም ማሳያ ነው -የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን
ሮቤ፤ ታሕሳስ 24/ 2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን እውን የሚያደርግና የአገሪቷን የዲፕሎማሲ ከፍታ የሚያሳይ መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ።
የተፈረመው ሥምምነት የሀገራቱን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክርና ታሪካዊ እንደሆነም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የተፈራረሙትን ሥምምነት በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራን እንዳሉት የመግባቢያ ስምምነቱ የባህር በር የማግኘት ፍላጎቷን እውን የሚያደርግና የአገሪቷን የዲፕሎማሲ ከፍታ የሚያሳይ ነው ።
ሥምምነቱ የኢትዮጵያን ተደማጭነት የበለጠ የሚያሳድግና የቀደመ ክብሯንና ታሪካዊ ሚናዋን ለመመለስ የሚረዳ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምራን መካከል ዶክተር መሐመድ ጀማል እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ለዓመታት ከባህር በር ባለቤትነት ተገልላ በመቆየቷ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ሰለባ አድርጓታል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረሙት ሥምምነት አገሪቷ በሰጥቶ መቀበል መርህ ዳግም የባህር በር የምታገኝበት መደላድል የሚፈጥር መሆኑን በማከል።
የመግባቢያ ሥምምነቱ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እውን የሚያደርግና የአገሪቷን የዲፕሎማሲ ከፍታ የሚያሳይ እንደሆነም አክለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሰጥቶ መቀበል መሪህ ከሶማሌ ላንድ ጋር ያደረገው ታሪካዊ ስምምነት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ሥምምነት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው መምህር ሙጂብ አብዱላሂ ናቸው።
አሁን የተደረሰው ታሪካዊ ሥምምነት ከአገር አልፎ ቀጣናዊ የንግድ ትስስር የሚያሳልጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚረዳ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎቷን እውን የሚያደርግ ስምምነት መፈራረሟ በዲፕሎማሲው ረገድ ትልቅ ስኬት እንደተገኘም ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የተፈራረሙ ሲሆን በስምምነቱ መሰረትም ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር የምትገነባ እንደሚሆን ተገልጿል።