ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሰጥቶ መቀበል መርህን ያከበረና የቀጣናውን ትብብር የሚያጠናክር ነው-አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሰጥቶ መቀበል መርህን ያከበረና የቀጠናውን ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታከናውነውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚደረግ ሙከራ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደመገዳደር እንደሚቆጠርም ጠቁመዋል፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወቃል፡፡

ስምምነቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ስምምነቱ ሰላማዊ ሂደትን የተከተለና የሰጥቶ መቀበል መርህን ያከበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ስምምነቱ የህዝቦችን በትብብር ማደግ የሚያረጋግጥና ማንንም የማይጎዳ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ትልቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ህዝብና በፍጥንት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ በተለይ የኢኮኖሚ እድገቷ ከወጪና ገቢ ንግድ ጋር የሚተሳሰር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም የወደብ ጉዳይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ህልውና መሆኑን በግልጽ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታከናውነው የትኛውም ሰላማዊ ጥረት በበጎ ጎኑ ሊወሰድና የትኛውም አካል ሊደግፈው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ስምምነት ከድህነት ለመውጣት የሚደረግ ጥረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ከብሔራዊ ጥቅም ጋር እንደሚተሳሰር አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት የምታከናውነውን ጥረት ለማደናቀፍ የሚደረግ ሙከራ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደመገዳደር እንደሚቆጠር ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበሩ ስራ ደግሞ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣናው የሚደረግ የኢኮኖሚ ትብብር የሰላም እንጂ የግጭት ምንጭ እንደማይሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ከሁለቱ ወገን ባለፈ ቀጣናውን በኢኮኖሚ፣ ቱሪዝምና ባህል ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና እንዳለውም ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሌ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑም ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም