ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ የተደረገው ጥሪ ኢትዮጵያን ለማወቅ እድል የሚፈጥር ነው - መሐመድ አል አሩሲ - ኢዜአ አማርኛ
ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ የተደረገው ጥሪ ኢትዮጵያን ለማወቅ እድል የሚፈጥር ነው - መሐመድ አል አሩሲ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ያቀረቡት ጥሪ የኢትዮጵያን ታሪክና ባህል ለማወቅ እድል የሚፈጥር መልካም አጋጣሚ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሰረት የዳያስፖራ አባላቱ ከታህሳስ 20 ቀን 2016 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሶስት ዙር ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ እየተሰራ ይገኛል።
የመጀመሪያ ዙር ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 20/2016 ድረስ የሚቆይ ሲሆን 'Connect to your multi culture' በሚል መሪ ሃሳብ ይከናወናል። ይህም ባህላቸውን እንዲያውቁና እንዲያስታውሱ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።
ሁለተኛው ዙር ደግሞ 'Connect to your history' በሚል መሪ ሀሳብ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ጀምሮ እስከ ክረምት መግቢያ የሚካሄድ ሲሆን በባህል፣ በቋንቋ እና በሃይማኖት ያሉ ታሪኮችን እንዲያውቁ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሶስተኛው ዙር 'Leave your legacy' በሚል ከ2016 ዓ.ም የክረምት መግቢያ ጀምሮ እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ህጻናትን በማስተማር፣ ችግኝ በመትከልና ሌሎች የክረምት በጎ ተግባራት መሳተፍ በሀገራቸው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ማድረግን ግብ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በውጭ ለሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ የተደረገበት ምክንያት፥ ሀገራቸውን እንዲያውቁ፣ እንዲወዱና በቀጣይ ጊዜ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ኢትዮጵያን እንዲያገለግሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ኢትዮጵያ በዓለም አድናቆት ካገኘችባቸው ባህሎቿ፣ ትውፊቶቿና የቱሪዝም መዳረሻዎቿ ባሻገር ሰፊ የልማትና የኢንቨስትመንት እድሎች ያሏት አገር መሆኗን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ የኢትዮጵያ ብዝኃ ባህሎችና እሴቶች እንዲሁም ያሏትን እምቅ ሀብቶች ለማወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
በተጨማሪም ዳያስፖራው ወደ አገሩ በመመለስ ያለውን ልማት እንዲመለከትና የስራው አካል እንዲሆን የሚጋብዝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዳያስፖራው የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና ምቹ ሁኔታዎች መፍጠሯን ጠቅሰው ዳያስፖራው ለአገሩ አምባሳደር በመሆን በልማት ስራዎች፣ በመልካምና ፈታኝ ወቅቶች ከአገሩ ጎን መቆሙንም ነው የምክር ቤት አባሉ ያወሱት።
ይህን በጎ ተግባር በማጠናከር ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በመጎብኘት አገራቸውን ማስተዋወቅ ከዳያስፖራው የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነም መሐመድ አል አሩሲ ተናግረዋል።
ለዚህም ሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ እንደ መልካም እድል በመጠቀም ወደ እናት አገራቸው በመምጣት ያሉ እድሎችን በመቃኘት ለኢትዮጵያ እድገት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሁለተኛው ትውልድ ዳያስፖራ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴ የዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁን መግለጹ ይታወቃል።