በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ምርጫ ተጠናቋል-ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮች ምርጫ ተጠናቋል-ኮሚሽኑ
ሰመራ ፤ታህሳስ 24/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ምርጫ ማጠናቀቁን አስታወቀ።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር አይሮሪት መሐመድ ዛሬ በሰመራ ሎጊያ ከተማ በሰጡት መግለጫ ተሳታፊዎችን የመምረጥ ሥራ ከህዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል።
የክልሉን አውድ ባገናዘበ መልኩ በተካሄደ ምርጫ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ 762 ተሳታፊዎችን ከተለያዩ ወረዳዎች በመለየት ምርጫው መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ባለፈው አንድ ወር በ48 ወረዳዎች ሲካሄድ የቆየው ተሳታፊ ተወካዮችን የመለየት ሂደት ስኬታማ ሁኖ መጠናቀቁንም ዶክተር አይሮሪት አመልክተዋል።
እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፣ በክልሉ በአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን ለመምረጥ በተዘጋጁ መርሀግብሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ከ3ሺህ 500 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።
በልየታ ሂደቱ ሽማግሌዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የንግድ ማህበረሰብ አባላትና ተፈናቃይ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ መደረጉንም አመልክተዋል።
ዶክተር አይሮሪት ለኮሚሽኑ ሥራ መሳካት የተባበሩ አካላትን፣ የመንግስት ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የብዙሀን መገናኛዎች እና ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
ኮሚሽኑ በመጪው ጊዜያት ለሚያከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ ተባባሪ አካላቱ የተለመደውን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የአፋር ህዝብና ባለድርሻ አካላት ለእስካሁኑ ያሳዮትን ተነሳሽነት ኮሚሽነሯ አድንቀው፣ በቀጣይም ሁሉም ለሀገራዊ ምክክሩ ሥራ ስኬታማነት የሚያበረክተውን አስተዋጾ እንዲያጠናከር አስገንዝበዋል።