የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሳደግ በስትራቴጅክ እቅድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የተሳካ ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሳደግ በስትራቴጅክ እቅድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች የተሳካ ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24/2016 (ኢዜአ)፦የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግስት ስትራቴጅክ እቅድ ወጥቶ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የተሳካ ውጤት እያስገኙ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ በተለይም በኢኮኖሚ ልማት የመንግስትን እቅድና እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት በዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በመንግስት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ስብራትን በመጠገን ምርታማነትን ለማሳደግ በመንግስት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅክ ዕቅድ ወጥቶ እየተሰራና ውጤትም እየተመዘገበበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ የእድገት ምንጭ ብዝኅ ዘርፍ እንዲሆን መደረጉ መሰረታዊ ለውጥ አምጥቷልም ብለዋል።
የግብርና፣ ኢንዳስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና አይ.ሲ.ቲ. እና ሌሎችም የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፎች የኢትዮጵያን እድገት በማሳለጥ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አብራርተዋል።
የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግርን ለማቃለልም በአጭርና መካከለኛ ጊዜ የግብርና ልማት ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።
በተለይም በበጋ የስንዴ መስኖ ልማት የተገኘው ምርት አስደናቂ መሆኑን የገለጹት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ የልማት ስራው በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የበጋ ወቅት 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ የስንዴ አዝእርት በመሸፈን ከ117 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታልሞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግም ዘመናዊ የእርሻ ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን በማቅረብ ለአርሶ አደሩ እገዛ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የዶሮ፣ ዓሳና የማር ምርቶች ላይ የተጀመረው ስራ ለበርካታ ዜጎች የገቢ አማራጭ እንዲፈጠር ማድረጉን ገልጸዋል።
የዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓት በመቀየር የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን በመቀነስ አገራዊ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ስራውን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ለግብርና ምርታማነት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።