በጋምቤላ ክልል የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት አሰራርን በተቋማት  ለመተግበር  የተጀመረው ስራ እንደሚጠናከር ተገለጸ

ጋምቤላ ፤ ታህሳስ 24 /2016(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል  ፍትሃዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት አሰራርን በተቋማት ለመተግበር  የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ  ፕላንና ልማት ቢሮ ገለጸ። 

ቢሮዉ አንድ እቅድ አንድ ሪፖርት አዘገጃጀት ዙሪያ  ለአመራሮችና ለመረጃና ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል። 

የቢሮ ኃላፊው አቶ ጃክ ጆሴፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤  ቀደም ሲል በሴክተር መስሪያ ቤቶች ወጥነት ያለው የዕቅድ አዘገጃጀትና አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት  የጊዜና የሀብት ብክነትና የተዛባ ሪፖርቶች ይስተዋሉ ነበር።

ባለፉት ሁለት ዓመታት አንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት አሰራር ተግባራዊ በመደረጉ ውስን የሆነውን የህዝብና የመንግስት ሃብት እንዲሁም የጊዜ ብክነትን በማስቀረት ረገድ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የዜጎችን ፍትሃዊ የልማትተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ  የጊዜና የገንዘበ ብክነትን ለማስቀረት የተጀመረ በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ የተዘጋጀውም በአመራሩና በባለሙያው ዘንድ ቁልፍ በሆኑ የልማት ዕቅዶችና የሪፖርት አዘገጃጀት ላይ ያሉ ክፍተቶች ለመሙላትና በቀጣይ የተሻለ የአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት ዝግጅትን ለማሻሻል ያለመ  ነው ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተስሉዋች ቾል በሰጡት አስተያየት፤ የግንዛቤ ማስጨበጫው  ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት ፎርማት እንዲመሩ  የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ለአመራሩና ለባለሙያዎች በአንድ ዕቅድ አንድ ሪፖርት ዙሪያ የተፈጠረው ግንዛቤ በዕቅድ የተከናወኑ ሪፖርቶች እንዳይዛቡ የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ኡጁሉ ከሊ ናቸው። 

 የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ላለፉት ሁለት ቀናት ባዘጋጀው የአንድ እቅድ የአንድ ሪፖርት አዘገጃጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ከ120 በላይ የአመራር አባላትና  ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም