ቀጥታ፡

በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ ግንባታ ለውጥ ለማምጣት እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ ነው-- አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

ሐረር፤ ታህሳስ 24/2016  (ኢዜአ)፦በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ ግንባታ  ለውጥ ለማምጣት እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ። 

ሀገር አቀፍ የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በሐረር ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በመድረኩ እንዳሉት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በጸጥታና ደህንነት፣ በህግ አስከባሪ አካላት እና በዴሞክራሲ ተቋማት ላይ በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ተከናውነዋል።

በእዚህም አገሪቱ ገጥሟት የነበረውን ፈተና ከመሻገር ባለፈ በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች ላይ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከእዚህ በተጨማሪ የሪፎርም ሥራዎች የብልጽግና ጉዞን እውን እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት አፈ ጉባኤው፣ "በተቋማቱ የተጀመሩ የለውጥና የሪፎርም ሥራዎች በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሊስፋፉ ይገባል" ብለዋል።

ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እንደ አገር አካታች፣ አሳታፊና ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት  በሚደረጉ ጥረቶች የምክር ቤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ታገሰ አመልክተዋል።


 

ምክር ቤቱ በሀገር ደረጃ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽንን ተግባራዊ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎች መጀመሩን ጠቁመው፣ ይህም ህዝቡ በፍትህ፣ በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተሻለ መልኩ ለመመለስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውና  ለዚህም መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምክር ቤቶችም የህግ አወጣጥና የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን በሚጠበቀው ጥራትና መጠን  በማከናወን ህገ መንግስታዊ ተልዕኳቸውን በትጋት እንዲያሳኩ አሳስበዋል።

"ሰላምና ጸጥታን ማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነቱንና ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት፣ የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

እንዲሁም ብቁ፣  ነጻና ገለልተኛ የሆነ አገልጋይ ሲቪል ሰርቪስ መገንባት ምክር ቤቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩባቸው የሚገቡ  መሆናቸውን  አፈ ጉባኤው አመልክተዋል።

በመድረኩ በፍርድ ቤቶችና በፍትህ ተቋማት ትራንስፎርሜሽን ሂደት ላይ አሁን የተደረሰበት ደረጃና የሚታዩ የአፈጻጸም ጉድለቶች በጋራ እንደሚመከርባቸው ተገልጿል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጠቃላይ የደረሰበት የሥራ ደረጃ እና በቋሚ ኮሜቴ የተደረገ ክትትልም በሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተመላክቷል።


 

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው አገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ በጀመረችው መንገድ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ሁሉም አካላት በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የሥራ ቅንጅት መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

"የጋራ መድረኩ በአገሪቱ እርስ በርስ የተጣጣሙና የተመጋገቡ ህጎች እንዲወጡ ትልቅ ጠቀሜታ አለው" ያሉት አቶ ኦርዲን፣ ይህም የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነትና አብሮነትን ለማጠናከር ፋይዳው እንዳለው ገልጸዋል።

እንዲሁም በፌዴራልና በክልል መንግስታት የሚወጡ ህጎች እንዲናበቡና በመካከላቸው ክፍተትና ተቃርኖ እንዳይኖር የሚያግዝ እና ተቀራራቢ የአፈጻጸም ደረጃ እንዲኖር የሚያበረክተው ድርሻ የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፣ እንዲሁም የክልል እና የሁለቱ ከተማ መስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ-ጉባዔዎችም በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም