ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ከገና በዓል ጋር ተያይዞ የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት እየተሰራ ነው  

አዲስ አበባ ፤ታህሣሥ 24 / 2016 (ኢዜአ)፡-  ከገና በዓል ጋር ተያይዞ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ። 

የአዲስ አባባ ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የበዓሉን መቃረብ ተከትሎ የዘይት፣ የዱቄት፣ የስኳር፣ የቁም እንስሳትና የእንሳሳት ተዋፅኦዎች ፍላጎት ይጨምራል።

ይህንንም ተከትሎ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በተለይም በኅብረት ሥራ ማኅበራት   የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችንም በስፋት እንዲያቀርቡ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን  ጠቁመዋል።


 

ለአብነትም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ፈሳሽ ዘይት፣  ከ1 ሚሊየን 42 ሺህ በላይ ሊትር ፓልም ዘይት፣ 124 ሺህ በላይ ዶሮ እንዲሁም ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ ሽንኩርት በእሁድ ገበያዎች፣ በኤግዚቢሽኖችና በገበያ ማዕከላት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የቁም እንሰሳትና ሌሎች የእንሰሳት ተዋጽዖ አቅርቦት በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

ጎን ለጎንም የበዓሉን ግርግር በመጠቀም በሸቀጦች ላይ ያልተገባ ጭማሬ በሚያደርጉና ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ሸማቹ ማኅበረሰብ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው የሚሸጡ፣ ምርት የመደበቅና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ሲያጋጥመው ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ይህን የሚያደርጉ አካላትን እንዲከላከል አስገንዝበዋል።

የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ሌሎች ከሕገ-ወጥ ግብይት ጋር የተያያዙ ጥቁማዎችን ለቢሮው ለማድረስ በ8588 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ መስጠት እንደሚቻልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም