ቀጥታ፡

ግብጽ የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር አጀንዳ የውሃ ድርሻና ክፍፍል መልክ እንዲይዝ የምታደርገው እንቅስቃሴ ድርድሩ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኗል - አቶ ፈቅ አሕመድ

አዲስ አበባ ፤ ታህሣሥ 24/2016(ኢዜአ)፡- ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ይዘት የውሃ ድርሻና ክፍፍል መልክ እንዲይዝና የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ተፈጻሚ እንዲሆን የምታደርገው ጥረት ድርድሩ እንዳይሳካ ማድረጉን የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና የውሃ ዲፕሎማሲ አማካሪ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ገለጹ።

ተቋርጦ የነበረው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም በድጋሚ መጀመሩ የሚታወስ ነው።

ድርድሩ የተጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብድል ፋታህ አል ሲሲ ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረጉት ምክክር የግድቡን የውሃ ሙሌትና የውሃ አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል የደረሱትን መግባባት ተከትሎ ነው። 

ይሁንና ድርድሩ ለአራት ዙሮች በአዲስ አበባና ካይሮ ሲካሄድ ቆይቶ ያለ ስምምነት ተጠናቋል።

የግብጽ አቋም የኢትዮጵያን የወደፊት የመልማት ፍላጎት የሚገድብ፤ በሕግ ማዕቀፎች ላይ የተፃፉ አንቀጾችን የሚፃረር ሀሳብ በመሆኑ ድርድሩ ያለ ስምምነት ተቋጭቷል።

የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞችና የውሃ ዲፕሎማሲ አማካሪው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ፤ ኢትዮጵያ በድርድሩ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና የጋራ ልማት ላይ ያተኮረ ሀሳብ ማንጸባረቋን ገልጸዋል።

በአንጻሩ ግብጽ እኔ ብቻ ልጠቀም በሚለው አቋሟ አጀንዳዋን ለማስፈጸም ያስችለኛል ያለቻቸውን ጉዳዮች ማንሳቷን አመልክተዋል።

ግብጽ ሰጥቶ የመቀበል መርህንና የዲፕሎማሲ አካሄድ አለመፈለጓ የቅርቡን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የነበሩ ድርድሮችን ውጤታማ እንዳይሆኑ ማድረጓን ተናግረዋል።

የሶስትዮሽ ድርድሩ ላለፉት አምስት ዓመታት በውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲካሄድ መቆየቱን ነው አማካሪው ያወሱት።

የግድቡ አላማ ውሃ መያዝና መልቀቅ አይደለም ኃይል ማመንጨት ነው ያሉት አቶ ፈቅ ድርድሩ በኃይል ማመንጨት ላይ መሆን ሲኖርበት ትኩረቱን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ማድረጉን አመልክተዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘም የድርቅ መከሰት የሚታየው ወደ ግድቡ ከሚገባው የውሃ መጠን እንጂ ከሚወጣው አንጻር አይደለም ያሉት አማካሪው ግብጽ ግን ከሚወጣው ውሃ አንጻር ታይቶ ኢትዮጵያ ያከማቸችውን ውሃ መልቀቅ ይኖርባታል የሚለው ሀሳቧ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ግብጽ ድርቅን የማካካስ ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ብቻ እንዲሰጥ መፈለጓ መርሕ ያልተከተለና በጋራ ድርቅን የመቋቋም ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ውጪ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ግብጽ በተናጥል ባቀረበችው የውሃ አሞላል እቅዷ ከሕዳሴ ግድብ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንዲለቀቅላት ያቀረበችው ጥያቄ የግድቡን የውሃ አሞላልና አለቃቅ እንዲሁም የግንባታ ሂደት የማጓተት መሆኑን ነው አቶ ፈቅ ያስረዱት።

በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ኮታ ይቀመጥ ማለቷም የሶስትዮሽ ድርድሩ ወደ የውሃ ድርሻና ክፍፍል መልኩን እንዲቀይር የማድረግ እንደሆነ ጠቅሰው ኢትዮጵያ ይህን ሀሳብ እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ አሳውቃለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩ የውሃ ክፍፍልና ድርሻ መልክ እንዳይዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ነው የገለጹት።

የውሃ ክፍፍል ጉዳይ ድርድርም መካሄድ ካለበት የናይል ተፋሰስ አገራትን ባካተተ መልኩ በናይል ቤዚን ኢኒሺዬቲቭ የትብብር ማዕቀፍ ሊሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

የግብጽ የውሃ ክፍፍል ጥያቄ እ.አ.አ በ1929 እና 1959 የተፈረሙትን የቅኝት ግዛት ዘመን ውሎችን መሰረት ያደረገ መሆኑንና ይህን ኢትዮጵያ ያልነበረችበትን ስምምነት እንደማትቀበለውና ተገዢ እንደማትሆን ገልጸዋል። 

የሶስትዮሽ ድርድሩ እ.አ.አ በ2015 በካርቱም የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት ያደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ፈቅ ኢትዮጵያ በስምምነቱ አማካኝነት የግድቡን ስራ እያከናወነች ነው ብለዋል።

ይሁንና ግብጽ ኢትዮጵያ የግድቡ ውሃ ሙሌትና ግንባታ አስመልክቶ የምትወስዳቸው እርምጃዎች የተጠናጥል ናቸው በሚል አቤቱታ እንደምታቀርብ ገልጸዋል።

በመርሆች ስምምነት አንቀጽ 5 “ሶስቱ አገራት በውሃ አለቃቀቅና አሞላል መመሪያው ላይ ይስማማሉ፤የግድቡ ግንባታ በትይዩ ይካሄዳል" እንደሚል ጠቅሰው፤ ከዚህ ውጪ "ውሃ ለመሙላት ይስማማሉ" የሚል ሃሳብ የለም ብለዋል።

“የግድቡ ግንባታ በትይዩ ይካሄዳል" ማለት  ግድቡ ኃይል ማመንጫ በመሆኑ የውሃ አሞላል፣ አለቃቀቅና ኃይል ማመንጨትን ይጨምራል ነው ያሉት።

ግብጽ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስልቶችን በማምጣት የሶስትዮሽ ድርድሩን ለማጓተት እንደምትጠቀም ገልጸው ኢትዮጵያ ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት አዝማሚያዎችን አስቀድሞ በመተንበይ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትና የጋራ ልማትን በዘላቂነት ለማስፈን የናይል ቤዚን ሁሉን አቀፍ የትብብር ማዕቀፍ (ሲኤፍኤ) ወደ ትግበራ እንዲገባ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባት አማካሪው መክረዋል።

ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩ በስምምነት እንዲቋጭ የተለያዩ አስታራቂ ሀሳቦችን ማቅረቧንና ግብጽ ግን ድርድሩን የማስቀጠል ፍላጎት እንደሌላት ማሳወቋን መግለጿ የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

 

 

  

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም