ቀጥታ፡

በኮምቦልቻ ከተማ  ከአንድ ቢሊዮን ብር  በሚበልጥ በጀት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

ደሴ ፤ ታህሳስ 24 ቀን 2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በተመደበ  ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ  በጀት  የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ መሃመድአሚን የሱፍ ገለጹ። 

በከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ከንቲባው ለኢዜአ ተናግረዋል። 

በዚህም ለበጀት ዓመቱ  ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ  የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ፣ 15 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የአቅመ ደካሞች ምገባ ማዕከልና መኖሪያ ቤት፣ ድልድይና  አረንጓዴ ልማት፣ ይገኙበታል ብለዋል።


 

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ  በበጀት ዓመቱ  ውስጥ ለማጠናቀቅ በተያዘው ዕቅድ መሰረት  በጥራት እንዲፈጸም  ከወዲሁ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ከንቲባው አመልክተው፤ ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የጀመረውን ሁለተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ አቶ ሁሴን ሰይድ በሰጡት አስተያየት፤ በአካባቢያቸው ለተሸከርካሪ ምቹ መንገድ ባለመኖሩ በመስኖ የሚመረተውን ምርት ለገበያ ለማቅረብ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ከመሃል ከተማው አካባቢያቸው ድረስ  የመንገድ ግንባታ ሥራ መጀመሩ የረጅም ጊዜ ችግራቸውን ይፈታል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅም የአካባቢቸውን ነዋሪዎች  በማስተባበር ለመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።


 

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ዚነት መሃመድ፤ በአካባቢያቸው ነባሩ መንገድ በመበላሸቱና መሸጋገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ ሲቸገሩ እንደቆዩ ጠቅሰው፤ አሁን እየተሰራ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ምቹ መንገድ ባለመኖሩ በምጥ የተያዙ እናቶችን ወደ ሕክምና ተቋም ለማድረስም ሆነ ገበያ ለመሄድ ችግር እንደነበር አመልክተው፤  የመንገዱ ግንባታ ይሄን ችግራችንን ይፈታል ብዬ እጠብቃለሁ ብለዋል።

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ዓመትም አንድ ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውም ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም