ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ 

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ኢትዮጵያ መድን ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ዘጠኝ ነጥብ በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

በሁለቱ ሽንፈት ያጋጠመው ሲሆን በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶታል። በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቷል፤ በ8 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሌላኛው የዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ያገናኛል። 

አዳማ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ያሸነፈ ሲሆን በአንዱ ተሸንፏል፤ በሁለቱ ደግሞ አቻ ወጥቷል። በ13 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ8 ነጥብ በግብ ልዩነት ተበልጦ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በአንዱ ሲያሸንፍ በአራቱ አቻ ወጥቷል።

የፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ሻሸመኔ ከተማ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቻል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም