ቀጥታ፡

መልክዐ ምድራዊ አመላካች ምርቶችና ባህላዊና ማህበረሰባዊ እውቀቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2016(ኢዜአ)፦ መልክዐ ምድራዊ አመላካች ምርቶችና ባህላዊና ማህበረሰባዊ እውቀቶች የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ እንዲሁም የመብት ጥሰትን አስመልክቶ ከባለመብቶች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብና ከፍትሕ አካላት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሄዷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዳሉ ሞሲሳ፤ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ማህበረሰባዊ ሀብቶቿን በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ በመጠበቅ የሕግ ከለላ መስጠት የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነች ብለዋል።

ከዚህ አኳያም መልክዐ ምድራዊ አመላካች ምርቶች እንዲሁም ባህላዊና ማህበረሰባዊ እውቀቶች የተመለከቱ ረቂቅ አዋጆች ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲዘጋጁ መቆየታቸውን አመልክተዋል።

የመልክዐ ምድራዊ አመላካች ምርቶች (Geographical Indications) ረቂቅ አዋጅ የግብርናና የእንስሳት ሀብቶችና ውጤቶች ጨምሮ ሌሎች ሀብቶች ከሽያጭ በዘለለ የአዕምሯዊ ጥበቃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ እንዲያገኙ ከተለዩት መካከል ቡና፣ የሸኖ ቅቤ፣ የሐረርና የጅሩ ሰንጋዎች የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰው አዋጁ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አመልክተዋል። 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም የባለብዙ ፀጋ አገር መሆኗን ከግምት በማስገባት ባህላዊና የማህበረሰብ ዕውቀቶች ጥበቃ እንዲያገኝ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱንም ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።

ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች፣ የባህላዊ ሕክምና እውቀት፣ ጭፈራዎችና የማህበረሰብ እሴቶች በአዋጁ ጥበቃ ከሚደርግላቸው መስኮች እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል። 

በተለይም የባህላዊ ሕክምና እውቀት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ መደረጉ ለእውቀት ሽግግር ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጆቹ በአሁኑ ሰዓት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገመገሙ እንደሚገኝና በቀጣይ ግብዓት ታክሎባቸው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አዋጆቹ በ2017 ዓ.ም ፀድቀው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ቡናና ሌሎችም በመገኛ ቦታቸው ተለይተው የሚታወቁ የግብርና ምርቶችን በመልክዓ ምድር ምንጭ አመላካች (Geographical Indications) ስርዓት እንዲመሩ ማድረግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀትና የፓይለት ፕሮጀክት በቡና ምርት ላይ ማስጀመር የሚያስችል ፕሮጀክት በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን(በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት) በአዋጅ የተቋቋመው በ1995 ዓ.ም ሲሆን በ2022 ዓ.ም ፈጠራንና ኢኖቬሽንን በማበረታተት የፈጠራ ሀሳቦችን ወደ እሴት በመለወጥ ሂደት ለአገራዊ ብልጽግና ቁልፍ ሚና የሚጫወት በአፍሪካ ተምሳሌት የአዕምሯዊ ንብረት ተቋም የመሆን ራዕይ ይዞ እየሰራ ይገኛል።

አዕምሯዊ ንብረት ማለት በሰው ልጅ አእምሮ የሚፈጠሩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚመለከት ሲሆን እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች እንደማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በንብረትነት የሚታወቁበትን አግባብ የያዘ ስርዓት ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም