ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት ዘርፈ ብዙ ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም አለው - የዘርፉ ምሁራን 

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 23/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት የአገሪቱን ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የሚያጠናክር መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።  

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ከሶማሌላንድ ጋር በትላንትናው ዕለት ተፈራርማለች። 

የመግባቢያ ሥምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ናቸው የፈረሙት።

በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን፤ ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንደምታገኝ ተመላክቷል።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ሂደት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ የራሷን ወደብ በመገንባት ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ፋይዳ ያላቸው ጥቅሞች የምታገኝበት መሆኑን ነው ያነሱት። 

የምጣኔ ኃብት ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኒዮስ በርኸተስፋ፤ የመግባቢያ ሥምምነቱ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ኩነት መሆኑን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ እራሷ የምታለማው ወደብ ሲኖራት፣ የሸቀጥ ዕቃዎችን ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሰፊ አማራጭ ያስገኝላታል ብለዋል። 

ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሶማሌላንድም የገቢ ምንጭ እንደሚኖረው አንስተዋል።

ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ በሰላምና ደኅንነት ዘርፍ ያላትን አዎንታዊ ሚና ይበልጥ እንድታጠናክርም ዕድል ይሰጣታል ነው ያሉት የምጣኔ ኃብት ምሁራን ።

ኢትዮጵያ ሌሎች የባህር በር እንዲኖራትም የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።


 

ሌላኛው የምጣኔ ኃብት ምሁሩ አቶ ክቡር ገና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ እንድትሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሶማሌላንድ ጋር የተደረሰው ሥምምነት ተስፋ ሰጪና ኢትዮጵያ በባህር በር በኩል ተጨማሪ አቅም እንድትገነባ የሚያስችላት እርምጃ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይም ሌሎች የባህር በር አማራጮችን በማየት ተጨማሪ የወደብ አማራጮችን ለማስፋፋት የተጀመረው ጥረት ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ምክረ-ኃሳባቸውን ሰጥተዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም