ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት በጋራ የመልማት ፍላጎቷ ማሳያ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት በጋራ የመልማት ፍላጎቷ ማሳያ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ከሶማሌላንድ ጋር በትላንትናው ዕለት ተፈራርማለች።

የመግባቢያ ሥምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ናቸው የፈረሙት።

በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንደምታገኝ ተመላክቷል።

የመግባቢያ ሥምምነቱ ሂደት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የመግባቢያ ሥምምነቱን ተከትሎ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ለሚኒስቴሩ ሰራተኞችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

በመልዕክታቸውም የባህር በር አለመኖር በሎጂስቲክስ ዘርፍ በርካታ ክፍተቶች ፈጥሯል፤ አሁን ላይ የባህር በር ለማግኘት የደረሰችው የመግባቢያ ሥምምነት አንዱ ምንዳ ነው ብለዋል።

የባህር በር ከሉዓላዊነት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ጠቁመው፤ የባህር በር ለማግኘት የተደረሰው የመግባቢያ ሥምምነት ተግባራዊ ሲደረግ ለሎጂስቲክ አገልግሎት መሳለጥ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በመሆኑም ትላንት የተደረሰው ሥምምነት ታሪካዊና የኢትዮጵያ ስብራት የሚጠግን ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም እውን እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ያለች ሀገር መሆኗን ጠቁመው የኢኮኖሚ አቅሟን የሚመጥን የወደብ አማራጮ ማስፋት እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

ትላንት የተደረሰው ሥምምነትም የዚህ ፍላጎት አካል መሆኑን ገልጸው በቀጣይም የወደብ አማራጮችን የማስፋት ተግባራቱ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የትኛውንም የጎረቤት ሀገር ለመጉዳት ዓላማ እንደሌላትና ይልቁንም በጋራ የመልማት ጽኑ ፍላጎቷን ለማሳካት እንደምትተጋም ነው ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም