ቀጥታ፡

የባህር በር ስምምነቱ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ብሎም ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር የሚያጠናክር ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 23 /2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ብሎም ዓለም አቀፍ የንግድ ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ገለጹ።

የባህር በር የመግባቢያ ስምምነቱ በጥሩ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ ትልቅ ስኬት ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ስምምነት በትናንትናው እለት ከሶማሌላንድ ጋር ተፈራርማለች።

የመግባቢያ ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን፤ ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ የሚኖራት ይሆናል።


 

በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ የተደረሰው ስምምነት ለኢትዮጵያ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ብሎም ዓለም አቀፍ ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ በወደብ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ስትዳረግ መቆየቷን ጠቅሰው፤ የአሁኑ ስምምነት የነበሩ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይም የወጪና የገቢ ምርቶችን ንግድ በማሳለጥ ለአገራዊ የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

በቀጣናው የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብርንና በጋራ የመልማት ዕቅድን የሚያሳካ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የባህር በር ስምምነቱ በጥሩ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ  ትልቅ ስኬት መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር በሪሶ፤ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ላደረጉት የላቀ ጥረት አድንቀዋል።

የባህር በር ስምምነቱ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱም ባለፈ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብ እና የጦር ሰፈር በማልማት መጠቀም የምትችል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም