የባህር በር ለማግኘት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እድሎችን ለመጠቀም ምሁራን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የባህር በር ለማግኘት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እድሎችን ለመጠቀም ምሁራን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይገባል
ሀዋሳ፤ ታህሳስ 23/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እድሎቿን እንድትጠቀም ምሁራን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ አስታወቁ።
የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካና የኢትዮጵያ የባህር በር አማራጮች ላይ ያተኮረ ውይይት በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ እንደገለጹት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባላትና በማደግ ላይ ላለችው ኢትዮጵያ የባህር በር አስፈላጊነት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
የባህር በር ያላቸውና የሌላቸው ሀገራት በአለም አቀፍ መድረክ ያላቸው ተሰሚነት እኩል አለመሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የባህር በርን ለማግኘት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እድሎቿን እንድትጠቀም ምሁራን ከፍተኛ ድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል ብለዋል።
ዶክተር አያኖ አክለውም የኢትዮጵያ የባህር በርን ማግኘት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠንና አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ የሚያጋጥመውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም የባህር በርን የማግኘት ጉዳይ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄና የቀጠናው ጂኦፖለቲካል ፍላጎት በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት የፖለቲካል ሳይንስና የፍልስፍና መምህር አቶ አወል አሊ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስችሏት በርካታ ምክንያቶች እንዳሏት ተናግረዋል።
ጂኦ-ፖለቲካል ተፈጥሮ፣ ታሪካዊ እውነታ፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አለም አቀፍ ህጎችና የደህንነት ጉዳይ ከምክንያቶቿ ይጠቀሳሉ ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ የሃያላን ሀገራትን ትኩረት የሳበ መሆኑን የገለጹት ጥናት አቅራቢው የቀንዱ ቀጣና ጂኦ ፖለቲካ ጠቀሜታ ከሌሎች የአለም ሀገራት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ መሆኑ በራሱ ሌላኛው አመክንዮ እንደሆነ ገልጸዋል።
የባህር በር ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ አለም አቀፉን ማህበረሰብ መሞገት የሚያስችል ሰነድ ማዘጋጀት ጥያቄውን ግልጽ ማድረግና ጉዳዩን ህዝባዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ሁሉን አቀፍ ድርድርና ዲፕሎማሲ፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ድርጅቶችን መጠቀም፣ የሃይል ምንጭ ሽያጭን እንደመደራደሪያ መጠቀምና ከፍተኛ የምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ተሳትፎ የባህር በር የማግኘት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ ትክክለኛነት ከአለም አቀፍ ህግ አንጻርና የባህር በር ታሪካዊ ዳራን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።