በአማራ ክልል የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ሁለት ሺህ 741 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ሁለት ሺህ 741 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወሰነ
ባህርዳር፤ ታህሳስ 23 /2016 (ኢዜአ)፡- የአማራ ክልል የይቅርታ ቦርድ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ሁለት ሺህ 741 ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም አሰታወቁ።
ቦርዱ ቀደም ሲል በይቅርታ ከማረሚያ ቤት ወጥተው የነበሩና 3 ዓመት ሳይሞላቸው ሌላ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ 38 ግለሰቦች የተሰጣቸው ይቅርታ ተነስቶ በህግ እንዲጠየቁ መወሰኑም ተመልክቷል።
የቢሮ ሃላፊው አቶ ብርሃኑ ጎሽም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ቦርዱ ይቅርታውን ማድረግ የቻለው በቆይታቸው የባህሪ ለውጥ ያመጡና የቆይታ ጊዜያቸውን በአብዛኛው ማጠናቀቃቸውን በማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ቦርዱ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ለሁለት ሺህ 741 ታራሚዎች መስፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው በይቅርታ እንዲለቀቁ መወሰኑን አስታውቀዋል።
በይቅርታውም በሽብርተኝነት፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በሙስና፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና በመሰረተ ልማት ማውደም ተከሰው የተፈረደባቸውን እንደማያካትት ጠቅሰዋል።
የተሰጠው ይቅርታም ማረሚያ ቤት ውስጥ ምስጉን መሆን የሚያስገኘውን እድል ለማሳየትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለማመላከት መሆኑን ተናግረዋል።
በማያያዝም ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈጽመው የነበሩና በይቅርታ የተለቀቁ ግለሰቦች ሶስት ዓመት ሳይሞላቸው ሌላ ወንጀል በመፈጸማቸው የተሰጣቸው ይቅርታ ተነስቶ በህግ እንዲጠየቁ መወሰኑንም አመልክተዋል።
ይህም ይቅርታ የተሰጠው ግለሰብ ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀል የበደለውን ማሀበረሰብ መካስ እንጂ ተመልሶ ወደ ጥፋት መግባት ለተደጋጋሚ የህግ ተጠያቂነት የሚያጋልጥ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው ብለዋል።
ቦርዱ የሰጠው ይቅርታም ከዛሬ ጀምሮ ማረሚያ ቤቶች በሚደርሳቸው ደብዳቤ መሰረት ተፈፃሚ እንደሚሆን አስታውቀዋል።