በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2016 (ኢዜአ)፦ለህብረተሰቡ በዓልን በማስመልከት በስፋት የሚቀርቡ ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት ሀይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የገና በዓል የፊታችን እሁድ ታህሳስ 28 ቀን ይከበራል።
የእምነቱ ተከታዮችም በአሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ምግብ ነክ ከሆኑ ምርቶች በተጨማሪ ሌሎች ግብአቶችን ከተለያዩ የገበያ ማዕከላት በስፋት ይገበያያሉ ።
ኢዜአ ከገና በአል ጋር ተያይዞ ለሸማቾች በስፋት የሚቀርቡ ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን እያደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ቆይታ አድርጓል።
በባለስልጣኑ የእንስሳት ተዋጽኦ እና አልሚ ምግብ ዴስክ ሃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ምርቶች ጥራትና ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ለህብረተሰቡ በስፋት የሚቀርቡ ምርቶች በጤና ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በተለይም ከበአል ጋር ተያይዘው በስፋት ገበያ ላይ የሚውሉት የቅቤ ፣ማር እና ዘይት ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት መደረጉን ነው ያስረዱት።
ሸማቾች ከገና በአል ጋር ተያይዞ የሚሸምቷቸው ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ጥራታቸው የተጠበቀ መሆኑን በተገቢው መንገድ ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም ማህበረሰቡ ምርቶቹን ከህጋዊ ነጋዴዎች ሊገዛ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በአሉን በማስታከክ ባዕድ ነገሮች የተቀላቀሉባቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዳይሰራጩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
ህብረተሰቡ ምርቶቹን በተመለከተ አጠራጣሪ ነገሮች ካጋጠሙት በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ወይም ለጸጥታ አካላት አፋጣኝ መረጃ መስጠት አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።