በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶችን በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰትን መጨመር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶችን በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰትን መጨመር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2016(ኢዜአ)፦ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትና የጥምቀት በዓልን ትውፊት በስፋት በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰትን መጨመር እንደሚገባ ተጠቆመ።
ኢትዮጵያ 14 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አስመዝግባለች።
የገና በአል በድምቀት የሚከበርበት የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት እና የጥምቀት በዓላት በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዳሬክተር ዶክተር ዮሃንስ አድገህ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአለም ቅርስነት ያስመዘገበቻቸው ቅርሶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላ ነው።
ከነዚህ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነውና የገና በዓል በድምቀት የሚከበርበት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን እንደሚያስተናግድ አስታውሰዋል።
በዓሉ በሚከበርበት እለት የሚከናወኑ ሃይማኖታዊ ስርአቶችን እና ቅርሱን በዓሉን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች የበለጠ በማስተዋወቅ ቀጣይነት ያለው የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር መስራት ይገባል።
የገና በዓልን ለማክበር በቦታው በርካታ ቱሪስቶች ስለሚታደሙ የቅርሱን ሃይማኖታዊ ትውፊት፣ ታሪካዊ ዳራውንና ማህበራዊ አውዱን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
በተመሳሳይ በጥር ወር የሚከበረውና የአደባባይ በአል የሆነው የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱን የበለጠ በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰትን መጨመር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
እነዚህን ቅርሶች መጠበቅ፣ መንከባከብና የሚገኘውን ማህበራዊና ባህላዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሁሉም ዜጋ ድርሻ እንደሆነ ዶክተር ዮሃንስ አንስተዋል።
ቅርሶቹ ያላቸውን የቱሪስት መስህብነት በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር ምሁራን በጥናትና ምርምር፣ መንግስት ለቅርሱ ጥበቃ በማድረግ፣ የእምነቱ ተከታዮች ትውፊቱን ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚገባ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
ቤተ ጊዮርጊስ እና ቤተ መድሃኔአለምን ጨምሮ 11 ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናትን ያካተቱት የላሊበላ ቤተ እምነቶች እየሩሳሌምን ታሳቢ አድርገው በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በንጉስ ላሊበላ የስልጣን ዘመን መገንባታቸውን የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
እነዚህ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ1978 ዓ.ም የአለም ቅርስ ሆነው በዩኔስኮ መመዝገባቸውም የሚታወስ ነው።
የጥምቀት በዓልም በተመሳሳይ በ2012 ዓ.ም በአለም የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሃብት ነው።