ቀጥታ፡

ክልሉ ዝርያቸው ተሻሽሎ ለተከላ የተዘጋጁ ከ32 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን እየተንከባከበ ነው

ዲላ ፤ ታህሳስ 23/2016(ኢዜአ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዚህ ዓመት የሚተከሉ ከ32 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ፈልተው እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሰልጣን ገለጸ።

የተሻሻሉ ዝርያዎች የቡና ምርታማነትና ጥራትን ከማሻሻል በተጓዳኝ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ መሆኑም ተመላክቷል።

የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሰልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ዝርያዎች ዝግጅት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተለይ ያረጁትን በአዲስ የመተካቱ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው ባለፈው ዓመት ብቻ ከ37 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች መተከላቸውን አስረድተዋል።

ከተተከሉት ውስጥ በአማካይ ከ89 በመቶ የሚልቁት መጽደቅ መቻላቸውን በተደረገ የመስክ ዳሰሳ መረጋገጡን ጠቅሰው በተለይ የአረንጓዴ አሻራ በትኩረት በተከናወነባቸው አካባቢዎች የፅድቀት መጠኑ 92 በመቶን የተሻገረ መሆኑንም አብራርተዋል።

በተያዘውም አመት በ5 ሺህ ሄክታር ላይ አዲስ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም 216 ሺህ ሄክታር የሆነውን የክልሉን የቡና ሽፋን ወደ 221 ሺህ ሄክታር እንደሚያሳደግ አስረድተዋል።


 

ለዚህም ከ13 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተሻሻሉና የአካባቢ ዝርያዎችን ዘር በማፍሰስ ከ32 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ፈልተው  በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የተሻሻሉ ዝርያዎች የቡና ምርታማነትና ጥራትን ከማሻሻል በተጓዳኝ በአጭር ጊዜ ምርት እንደሚሰጡ ጠቅሰው ከችግኝ ዝግጅት በተጓዳኝ ከ923 ሺህ ቶን በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አማካይ የቡና ምርታማነትን በሄክታር ከ7 ነጥብ 5 ኩንታል ያልዘለለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና የጥራት ቁጥጥር ዘርፍ ሃላፊ አቶ አዲሱ መኮንን ናቸው።

ይህም ከዓለም የቡና አምራች ሃገሮች አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው የተሻሻሉ ዝርያዎች አቅርቦትና ዘመናዊ አሰራር አለመከተል ለምርታማነት ማነስ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

በክልሎች የተጀመረውን የተሻሻሉ ዝርያዎች ልማትን ለማስፋት አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ይህም አማካይ የቡና ምርታማነትን በአጭር ጊዜ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በጌዴኦ ዞን የኮቾሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋሻው በቀለ፤ በበኩላቸው በወረዳው ከ12 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በቡና እየለማ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 40 በመቶው በእርጅናና በበሽታ ምክንያት ምርት የማይሰጥ መሆኑን ገልፀዋል።

ሆኖም በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ያረጁ የቡና ዛፎችን በአዲስ በመተካት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል።

ይህንን ለማሳካት በተያዘው ዓመት ከ1 ሺህ 300 ሄክታር በላይ ያረጀ የቡና ዛፍ ያለበትን አካባቢና አርሶ አደሮችን በመለየት በልማት ባለሙያዎች የታገዘ የነቀላ ስራ በዘመቻ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ለዚህም በመንግስትና በተደራጁ ኢንተርፕራይዞች እጅ በሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎች ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በወረዳው የብሎያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አዲሱ ጠካሞ በበኩላቸው ከሁለት ሄክታር በላይ የቡና ማሳ ቢኖራቸውም በእርጅና ምክንያት የሚያገኙት ምርት ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው አመትም ያረጀ ቡና አንስተው በምትኩ 3 ሺህ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም