ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት በጥሩ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ ትልቅ ስኬት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት በጥሩ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ ትልቅ ስኬት ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት በጥሩ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ ትልቅ ስኬት መሆኑን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ስምምነት በትናንትናው እለት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራርማለች።
የመግባቢያ ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የተፈራረሙ ሲሆን በስምምነቱ መሰረትም ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር የምትገነባ ይሆናል።
የመግባቢያ ስምምነቱ ሂደት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ የሚገባ ሲሆን ስምምነቱ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑም ተመላክቷል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር በሪሶ አመሎ፤ የባህር በር ስምምነት በጥሩ የዲፕሎማሲ ጥረት የተገኘ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
የተደረሰው ስምምነት ታሪካዊና የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚያስቀጥል መሆኑን ጠቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላደረጉት የላቀ የዲፕሎማሲ ጥረት አድንቀዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር ስምምነት ለዘመናት የተቆለፈን በር የሚከፍትና የኢትዮጵያን የኮኖሚ እድገትና ብልጽግና የሚያረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር በማልማት መጠቀም የምትችል ይሆናል።