የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ይጠናከራሉ- ከንቲባ ከድር ጁሀር - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ይጠናከራሉ- ከንቲባ ከድር ጁሀር
ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 23/2016 ( ኢዜአ) በድሬዳዋ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስ የተተገበሩ ውጤታማ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ተናገሩ።
ሪፎርሙ መተግበሩን ተከትሎ በየተቋማቱ የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተገልጋዮች ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በድሬዳዋ አስተዳደር ጥናትን መሰረት በማድረግ በሁለም የመንግስት ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በፍጥነት በመፍታት በኩል ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን አመራሮችና ተገልጋዮች ለኢዜአ ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ሪፎርሙን ተከትሎ በአሠራር፣ በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ላይ በተደረጉ ለውጦች በየተቋማቱ የህዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች በፍጥነትና በጥራት ለመመለስ የተጀመሩ ሥራዎች ጅምር ውጤት እያስገኙ ናቸው።
በእዚህም በተለይ ህዝብ የአገልግሎት አሰጣጥን የሚያማርርባቸው ሴክተሮች እና የቀበሌ አስተዳደሮች ተለውጠው የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ ነው ብለዋል።
የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነትና በጥራት የማጠናቀቅ ጅምር ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑንም ከንቲባ ከድር አስታውቀዋል።
በቅርቡ ለከፍተኛ አመራሩና በየደረጃው ለሚገኙ ሠራተኞች በአገር ወቅታዊ ጉዳዮችና በአገልግሎት ማዘመን ላይ የተሰጠው ስልጠና በሪፎርም አተገባበር በድሬዳዋ የተስተዋሉ ለውጦችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ለገሰ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በሦስት ዙር በሁሉም ተቋማት የተተገበረው ሪፎርም በልማት፣ በሰላም፣ በፕሮጀክቶች አተገባበርና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ ለውጦች ለማምጣት አስችሏል።
በተለይ በቴክኖሎጂ የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋቱ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ማገዙን ነው የተናገሩት።
የንግድ ፍቃድ ዕድሳትና የመታወቂያ ካርድ አገልግሎት ፈልገው የመጡት አቶ አብዱሰመድ አልይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በቀበሌው ፈጣን አገልግሎት በማግኘታቸው ተደስተዋል።
ቀደም ሲል ለመታወቂያ ካርድ ሳምንት መመላለስና የሥራ ጊዜን ማባከን የተለመደ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም በየመንደሩ ለሚስተዋሉ የመንገድና የውሃ ችግሮች ቀበሌው ፈጣን ምላሽ መስጠት አለበት ብለዋል።
የንግድ ፍቃድ ለማደስ የመጡት አቶ አንዱአለም ዘሪሁን እንዳሉት፤ በቴክኖሎጂ የታገዘው የአሠራር ለውጥ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት ለነዋሪዎች ለመስጠት እያገዘ ነው።
ሪፎርሙ የበለጠ ለውጥ እንዲያመጣ ከኔትወርክ መቋራረጥ ጋር ለሚስተዋሉ ክፍተቶች መፍትሄ መፈለግና ተቀናጅቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
የቀበሌ 03 አስተዳደር ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሁሴን አብዶ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ሪፎሙን በተቀናጀ መንገድ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ በቀበሌ የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ከፍጥነትና ከጥራት አንጻር ለውጦች ታይተዋል።
ይሁን እንጂ በኔትወርክ መዛባት እና መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየታችን በቅርቡ መፍትሄ ይበጅለታል ብለዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት በተተገበረው የሪፎርም አሠራር ሂደት የተገኙ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በመገምገም የተሻለ ውጤት ለማምጣት የጥናት ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ መግባቱ ታውቋል።