በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የአየር ትንበያና የምርምር ስራ የሚከናወንበት ዘመናዊ ህንፃ እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የአየር ትንበያና የምርምር ስራ የሚከናወንበት ዘመናዊ ህንፃ እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2016(ኢዜአ)፦ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተደራጅቶ የአየር ትንበያና የምርምር ስራ የሚከናወንበት የዘመናዊ ህንፃ ግንባታ በመገባደድ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለዋና መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ቦሌ እያስገነባ ያለው ዘመናዊ ህንጻ ግንባታው ከ86 በመቶ በላይ ደርሷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የግንባታውን ሁኔታ ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፤ የግንባታውን አጠቃላይ ክንውን በተመለከተ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከመሬት በላይ 9 ወለል እና ከመሬት በታች 2 ወለል ያላቸው ሶስት ህንጻዎች ያሉት ሲሆን አሁን ላይ ግንባታው ከ86 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል።
እየተገነባ ያለው ህንፃ ለስራ ምቹ የሆነ፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዙ መሰረተ ልማቶች የሚሟሉለት የተፋጠነ እና ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል እንዲሁም የምርምር እና ስልጠና ስራ የሚከናወንበት መሆኑን አቶ ፈጠነ አብራርተዋል።
የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳር፣ የከፍታ አየር መመዝገቢያ ጣቢያዎች፣ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ኮምፒውተሮችን በመጠቀም የሚሰራውን ስራ የበለጠ የሚያጠናከር ሲሆን ለሰው አልባ የሜቲዎሮሎጂ መረጃ አሰባሰብ ስራም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአቬዬሽን ዘርፍ፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤና እና ሌሎችም አገልግሎቶች የተሟላ መረጃ ለመስጠት ኢንስቲትዩቱ የተጠናከረ ስራ የሚያከናውን መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ጽህፈት ቤት ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ መስሪያ ቤቱ ለዓለም አቀፍ የመረጃ ልውውጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
የአፍሪካ ሚቲዎሮሎጂ ተቋማት የሚሰለጥኑበትና ልምድ የሚወስዱበት ማእከል ስለሚሆን የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማጠናከርና ለወጭ ምንዛሬ ግኝት የሚጠቅም ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ መስኖ፣ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፈቲያ አህመድ፤ የተቋሙ መገንባት ሀገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ የሚኖረው መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ለግንባታው መፋጠን የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።