ለሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት ትግበራ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት ትግበራ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦ ለሰቆጣ ቃልኪዳን ስምምነት ትግበራ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ2015 ዓ ም አፈጻጸም፣ 2016 ዓም ዕቅድ እና የምግብ ትራንስፎርሜሽን ማስተዋወቂያ መድረክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተደድሮችና ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል በ2007 ዓ.ም በሰቆጣ ከተማ የተደረሰው የሰቆጣ ቃልኪዳን ሥምምነት በተወሰዱ እርምጃዎች፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮረ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ያልተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነት ችግሮች በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ይጠይቃል።
እስካሁን 240 ወረዳዎችን በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀው፣ በ2016 በጀት ዓመት ተጨማሪ 94 ወረዳዎች በሰቆጣ ስምምነት ትግበራ ለማካተት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ለሥምምነቱ ትግበራም አመራሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከስርዓተ ምግብ ችግሮች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ አግባብ ለመሥራት የሚያስችል ምክር ቤት ለማቋቋም ዝግጅት ተጀምሯል።
ምክር ቤቱ በአጭር ጊዜ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊው ርብርብ ይደረጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም የባለድርሻ አካላት ያልተቆጠበ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው መቀንጨር እና ተያያዥ ችግሮች ከመሰረቱ ለመፍታት እንደ አገር የተመጣጠነ ምግብ ይዘት ያላቸው ግብርና ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋት፣ አረንጓዴ ልማት እና ብሔራዊ ስንዴ ልማት ሀገራዊ መርሃ ግብሮች ይህን ግብ ለማሳካት አጋዥ እንደሆኑ ተናግረዋል።
የምርት ብክነት፣ የቴክኖሎጂ እጥረት እና መሰል ማነቆዎችን በትብብር መቅረፍ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ላለፉት ዓመታት በሰቆጣ ቃል ኪዳን በተተገበረባቸው ወረዳዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ተሞክሮዎችን በሌሎች ወረዳዎችን በማስፋት ብርቱ ሥራ እንደሚጠይቅም ነው የተናገሩት፡፡
በተለይም እናቶችና ህጻናትን ተደራሽ ለማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
በጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በ2015 ዓ.ም በሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት ትግበራ ከሁለት ዓመት በታች የሆናቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የዕድገት ክትትልና አገልግሎት ተሰጥቷል።
እንዲሁም 789 ሺህ 108 ነፍሰ ጡር እናቶችን የአይረን እንክብል የተሰጠ ሲሆን ከ488 ሺህ በላይ ቤተሰቦችን በጓሮ አትክልት፣ለነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች የወተት ፍየሎችና ዶሮዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
በትምህርት ቤት ምገባ፣ በንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ በንጽህናና ሳኒቴሽን ተደራሽነት ረገድ ስኬታማ ክንውን መኖሩም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።