ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ስርዓት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ስርዓት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016 (ኢዜአ) የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ የጤና መድህን ስርዓት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።
ሁለተኛው ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ተካሄዷል።
በስብሰባውም የብሄራዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን ጨምሮ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተወካዮች፣ የክልል ጤና እና ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊዎች፣ እና የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ሃላፊዎች እና ተወካዮች የተሳተፉ ተሳትፈዋል።
በዚህ ስብሰባም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የ2015 አፈጻጸም ሪፖርት፤ የ2016 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሁም፤ የገቢ ሁኔታን መሰረት ያደረገ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አመታዊ የመዋጮ መጠን እና የፌደራልና የክልል የቋትና የሪዘርቭ ፈንድ ድርሻ በመወሰን የትግበራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ዓላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ ደመቀ መኮንን ከዓመት ዓመት የአባላት ምዝገባና እድሳት ሽፋናቸውን በጥሩ ሁኔታ የቀጠሉ ክልሎችና ወረዳዎች ስኬት ዋነኛ ምክንያት በየደረጃው ያለው አመራር ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል መኖር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በ2016 የጀት ዓመትም ፕሮግራሙ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆንና ቀጣይነት ባለው መልኩ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብሎም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ከክልላዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ አመራሩ ለፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥቶ በባለቤትነት መምራት፣ መደገፍና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርበትም አክለዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው የጤና መድህን መርሃ ግብር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብሎም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ከክልላዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ አመራሩ ለፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥቶ በባለቤትነት መምራት፣ መደገፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ መርሃ ግብርም በሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች በተሰጠው ትኩረት እና ርብርብ፤ በ2014 በሃገር አቀፍ ደረጃ ከነበረው 894 ወረዳዎች ወደ 1022 ወረዳዎች በማካተት
ወደ 12 ሚሊዩን የሚጠጉ አባወራዎች እና እማወራዎችን አባል በማድረግ ባለፈው አመት ከነበረው በ10 ሚሊዮን ቀጠቃሚዎች ያለው ሲሆን በዚህ ዓመትም 55 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን እንዲያገኙ ማድርግ መቻሉን ዶክተር ሊያ ታደሰ መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚህም የባለፈው ዓመትን ተሞክሮ በማዳበር በዚህ በጀት ዓመትም በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የጤና መድህን ሽፋን በማሳደግ የጤና መድህን ትግበራ በየደረጃው ያለው የፖለቲካ አመራሩን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የማህበረሰብ ጤና መድህን የሚተገብሩ ወረዳዎች ሽፋን ወደ 90 በመቶ ማሳደግ፣ የማህበረሰብ ንቅናቄ በማድረግ በማህበረሰብ ጤና መድህን የሚታቀፉ ቤተሰቦች ሽፋን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
በየደረጃው ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እንዲሻሻል በማድረግ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት አጠቃቀም እንዲጎለበት ማድረግ እንደሚገባ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናግርዋል።