ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራረመች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሌ ላንድ ጋር ተፈራረመች።
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር የምትገነባ ይሆናል።
ስምምነቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቱ ሂደት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባም ተገልጿል።
በተጨማሪም ስምምነቱ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚ አለመሆኗ ለዘመናት ትልቅ ስብራት ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
የዛሬው ስምምነትም ይህን ስብራት በመቅረፍ ረገድ ታሪካዊ መሆኑን አብስረዋል፡፡
ይህ የመግባቢያ ሰነድ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ እና ለጋራ ጥቅም ከጎረቤቶቿ ጋር የመስራት ፍላጎት እና አቋሟን መልሶ የሚያፀና መሆኑን ጠቅሰው፤ ለመላ ኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ሁለቱንም ወገኖች በልማት በማስተሳሰር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን፤ በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር በማልማት መጠቀም እንደምትችል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጤና ፣ ትምህርት፣ በባህል፣ ግብርና ፣ ንግድ፣ መሰረተ ልማት እንዲሁም በወታደራዊ ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሰረትም ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሶማሌ ላንድ በኩል ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ እንድታገኝ በስምምነቱ መመላከቱን ጠቅሰው፤ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በቀጣይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የመግባቢያ ስምምነት ሂደቱ በቀጣይ አንድ ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናግረዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱ ለአፍሪካ ቀንድ ትሥሥር የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑንና ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እና ደህንነት የሚገባትን ሚና እንድትጫወት የተሻለ እድል የሚፈጥር መሆኑም ተመላክቷል።