በከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች በመንግሥት የማሻሻያ ሥራዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች እየተፈቱ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦በከሰም ስኳር ፋብሪካ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች በመንግሥት የማሻሻያ ሥራዎችና የመፍትሔ አቅጣጫዎች እየተፈቱ መሆኑን የፋብሪካው አመራሮች ገለጹ።

በአፋር ክልል በዞን ሦስት አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች በከሰም ቀበና ሸለቆ የሚገኘው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከአዲስ አበባ 250 ኪሎ ሜትር ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ደግሞ በ50 ኪሎ ሜትር ይርቃል።


 

የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ የማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ካለው ርቀትና አዋጪነት አንፃር እንደገና ተጠንቶ ራሱን ችሎ እንዲቋቋም ተደርጓል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ 123 ሚሊዬን ዶላር ብድር "ኮምፕላንት" በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባ ሲሆን፤ በ2007 ዓ.ም የመጨረሻ የሙከራ ምርቱን አጠናቆ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ መደበኛ ሥራ መጀመሩ ታውቋል።

በ2007 ዓ.ም የሙከራ ሥራውን አጠናቆ በ2008 ወደ ሙሉ ምርት ሲገባ በወቅቱ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች እንደነበሩ የፋብሪካው የኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈጠነ ዳባ ይናገራሉ።

የመሠረተ-ልማቶች አለመሟላት፣ የመሬት ይዞታ ባለመረጋገጡና በቀድሞ የውሃ መስኖና ኢነርጂ (በአሁኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር) የተጀመሩ ሥራዎች ባለማለቃቸው ፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ እጥረት ያጋጠመው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ በቀን 60 ሺህ ኩንታል ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት 6 ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም ቢኖረውም በግብአት እጥረቱ የሚፈለገውን ምርት ማሳካት አልቻለም ሲሉ ይናገራሉ።

በመሆኑም የሸንኮራ አገዳ ምርት አቅርቦቱን ችግር ለመፍታት ከአሚባራ እርሻ ልማት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር ውይይት በማድረግ አቋርጦት የነበረውን የሸንኮራ አገዳ ልማት በድጋሚ ማምረት መጀመሩን ጠቁመዋል።

በእርሻ ልማት ብቻ ሲከናወን የነበረውን የአገዳ ተከላ የፋብሪካው ሠራተኞች በዘመቻ የአገዳ ተከላ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።

በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንዲችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ የእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ጋኖ፤ የፋብሪካውን የማምረት አቅም ለማሳደግ የመሬትና የፋይናንስ ኃብት የማፈላለግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ፋብሪካው ከሚያርፍባቸው አዋሽ ፈንታሌ እና ዱለቻ ወረዳዎች ጋር በመነጋጋር ምርታማነትና አቅርቦትን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።

በአምስት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት የፋብሪካውን የአገዳ ግብአት ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ የከሰም ስኳር ፋብሪካ በቂ ዝግጅቶች ሳይደረጉ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉንና የፋይናንስና አስተዳደራዊ ችግሮችም ገጥመውት መቆየቱን አስታውሰዋል።


 

በመሆኑም ባለፉት 18 ወራት መንግሥት ባደረጋቸው የማሻሻያ ሥራዎች የግብዓት አቅርቦትና የይዞታ ችግሮች እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ተናግረዋል።

በስኳር ፋብሪካዎች ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት የተደረጉ የማሻሻያ ሥራዎች ለውጦች እየተመዘገበባቸው ይገኛልም ብለዋል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ በመጀመሪያ ምዕራፍ ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ 1 ሚሊየን 530 ሺህ ኩንታል ስኳር እና 12 ሚሊየን 500 ሺህ ሊትር ኢታኖል በዓመት ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።

የማስፋፊያ ሥራ ሲደረግለትም ፋብሪካው በዓመት 2 ሚሊየን 600 ሺህ ኩንታል ስኳርና 30 ሚሊየን ሊትር ኢታኖል ሊያመርት የሚችል መሆኑን የኢትዮጵያ ስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ መረጃ ያመለክታል።

የከሰም ስኳር ፋብሪካ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ  ቁጥር 497/2014 ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ከተደረጉ አምስት የስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም