ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በዛሬው ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ ፈርመዋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ሰነድ ፈርመዋል።

የኢፌዲሪ መንግስት እና የሶማሌላንድ መንግስት የፈረሙት የትብብር እና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ በተለያዩ ዘርፎች በቀጣይ ለሚኖር ግንኙነታቸው ማዕቀፍ እንደሚሆን ተመላክቷል።


 

ይህ የመግባቢያ ሰነድ የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት እውን የሚያደርግ፣ የባህር በር አማራጮችን የሚያሰፋ፣ የሁለቱን ወገኖች የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የፀጥታ እና የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናከር ነው።

እንዲሁም ሰነዱ በፖለቲካ እና በዲፕሎማሲ ዘርፍ የሚኖራቸው ግንኙነት የሚጎለብትበትን አካሄድ የሚያካትት ነው።

ይህ የመግባቢያ ሰነድ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ እና ለጋራ ጥቅም ከጎረቤቶቿ ጋር የመስራት ፍላጎት እና አቋሟን መልሶ የሚያፀና እንደሆነም ተገልጿል።

ሰነዱ አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት እና ለአፍሪካ ቀንድ ትሥሥር የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑንና ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እና ደህንነት የሚገባትን ሚና እንድትጫወት የተሻለ እድል የሚፈጥር መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም