ቀጥታ፡

የህዝብ ጤናን በማሻሻል የበለጸገ ማህበረሰብ ለማፍራት በትብብር በተሰሩ ሥራዎች ውጤት እየተገኘ ነው

ሰመራ ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦ የህዝብን ጤና በማሻሻል የበለጸገ ማህበረሰብ ለማፍራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በተሰሩ ሥራዎች ውጤት እየተገኘ መምጣቱን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዮቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም በሰመራ ከተማ እያካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ እንዳሉት፤ እንደአገር የህዝብ ጤና በማሻሻል የበለፀገ ማህበረሰብ ለማፍራት ኢንስቲቲዮቱ ከጤና ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው።

ባለፉት ጊዜያት ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ቢገጥሙም ለህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ትኩረት በመሰጠቱ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በየጊዜው የጤና ክስተቶችን ለመለየት ቅኝት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ቅኝት የሚደረግባቸው የጤና ክስተቶችም ከ21 ወደ 36 እንዲያድጉ መደረጉን ጠቁመዋል።

በቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ህዝብን ቀድሞ በማንቃት፣ ቀድሞ በመተንበይ፣ የጤና ስጋቶችን በመለየትና  የህብረተሰብ ጤና ቁጥጥሩን በማዘመን በተሰሩ ሥራዎች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አስረድተዋል።

የዓለም ስጋት የሆነውን የተህዋስያን መድኀኒት የመላመድ እና የስርጭት አድማስን ለመከላከል በተለያዩ ክልሎች የተወሰኑ ቦታዎች የቅኝት ሥራዎች መከናወናቸውንም ዶክተር መሳይ ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከኮሮናቫይረስ፣ ከኢንፍሎዌንዛ እና ጉንፋን መሠል በሽታዎች ጋር በተያያዘ ከብሔራዊ ላቦራቶሪ ጋር ሥራዎች በቅንጅት መከናወናቸውንም አስታውቀዋል። 

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ በተለያዩ ምክንያት የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደርስባቸውን የስነ ልቦና ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎችም በኢኒስቲትዩቱ በኩል ተከናውነዋል።

በሽታዎች ከመከሰታቸው ቀድሞ የመከላከልና ከተከሰቱም በኋላ የመረጃ ልውውጥ ሥራዎችን በቅንጅት የሚከታተል ግብረ ሀይል በማቋቋሙ ሥራዎች መሰራታቸውንም አብራርተዋል።

በዓለም አቀፍ ጤና ደንብና ህግጋት መሠረት ወደ ሐገር ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ ተጓዦች ላይ የበሽታ ቁጥጥር ሥራ መከናወኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ "ባለፈው ዓመት ብቻ 2 ሚሊዮን ተጓዦች ላይ የበሽታ ቁጥጥርና ልየታ ሥራዎች ተከናውነዋል" ብለዋል።

ከዚህ በፊት በውጭ አገራት ከሚደረጉ ምርመራዎች አብዛኞቹ በአገር ውስጥ መመርመር እንደተቻለ ጠቁመው፣ ይህንን ለማሳደግ የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው፣ ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ የተከሰቱ ወረርሽኞችን ለመከላከል ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።


 

በእዚህም የኮሌራ እና የወባ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ተችሏል ብለዋል።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አቶ ዊቲካ ኖሬ በበኩላቸው መንግስት ለጤናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠቱ በክልሉ ተከስተው የነበሩ ወረርሽኞችን መከላከል እንደተቻለ ተናግረዋል።

ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ ተመላክቷል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም