ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ እየተደረገ ነው - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት

አሶሳ ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ እንዲገቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

በክልሉ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማነቃቃት ያለመ መድረክ ዛሬ በአሶሳ ተጀምሯል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲነቃቃ ከእደጥበብ ጀምሮ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በቴክኖሎጂ እና በእውቀት እየደገፈ ነው፡፡

የተቋሙ ዋና ሃላፊነት አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ እንዲገቡ መደገፍ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እምቅ አቅም ያለው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በክልሉ የቀርከሃ፣ የእንስሳት፣ የአሳ፣ የወርቅ እምነበርድ እና ሌሎችም ሃብቶች እሴት ተጨምሮባቸው እስከ ውጪ ገበያ እንዲውሉ ጠንካራ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር መነሻ ገንዘብ እና የማምረቻ መሳሪያዎችን በብድር እና በሊዝ እንዲያገኙ ከማድረግ ጀምሮ አስፈላጊው እገዛ እንደሚያደረግ አመልክተዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው በክልሉ ኢንተርፕራይዞችን በማንቀሳቀስ ረገድ የተገኙ ውጤቶች ቢኖሩም ካለው የተፈጥሮ ሃብት አንጻር በሚፈለገው ልክ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡


 

አምራች ኢንዱስትሪው በሃገር ኢኮኖሚ ውስጥ የጎላ ሚና አለው የሚሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን በማብዛት የሃገሪቱን የብልጽግና ጉዞ መደገፍ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም የተፈጥሮ ሃብቱን በሚገባ በማልማት ህብረተሰቡን ከድህነት ለማውጣት የክልሉ መንግስት በትጋት ይሰራል ብለዋል፡፡

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቃሲም ኢብራሂም በበኩላቸው በክልሉ እስካሁን 102 አምራች ኢንዱስትሪዎች በእንጨት፣ ብረታ ብረት፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳት፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኮንስትራክሽን እና ሌሎችም ዘርፎች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

የግብዓት እና ጥሬ ምርት አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የማምረቻ እና መሸጫ ቦታ ምቹ ማድረግ እና ካፒታል አቅም ማጎልበት በቀጣይ ትኩረት ተደርገው የሚሰሩ ጉዳዮች እንደሚሆኑ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት እና የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ በጋራ ባዘጋጁት በዚሁ መድረክ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ዶክተር ተመስገን ዲሳሳን ጨምሮ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም