ቀጥታ፡

በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ጎርፍን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፤ ታህሣሥ 22/2016(ኢዜአ)፡- በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ጎርፍን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በአፋር ክልል እየተከናወኑ ያሉ የበጋ መስኖና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በተመለከተ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ቅኝት እያደረገ ነው። 


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ መንግሥት ሕብረተሰቡን በማስተባበር በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ጎርፍን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እያከናወነ ነው። 

ጎርፉን በዘላቂነት ለመከላከል በአሚባራና ፈንታሌ ወረዳዎች አዋሳኝ የሚሠራው የአዋሽ ወንዝን አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል። 

የአዋሽ ተፋሰስ ዘርፈ-ብዙ አገልግሎት መስጠት የሚችል፣ የመልማት አቅምን በእጅጉ የሚያሳድግ የኢትዮጵያ ጸጋ ቢሆንም በደራሽ ጎርፍ ምክንያት መቶ ሺዎችን እያፈናቀለ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነባቸው አጋጣሚዎች ተከስተው ያውቃሉ ብለዋል። 

በመካከለኛውና ታችኛው አዋሽ ተከስቶ የነበረው ድንገተኛ ጎርፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎችን አፈናቅሎ እንደነበርም አስታውሰዋል። 

በመሆኑም መንግሥት ችግሩን በአጭርና በረዥም ጊዜ የጎርፍ መከላከል ሥራ ለመፍታት የተግባር እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል። 

በአሚባራና ፈንታሌ ወረዳዎች አዋሳኝ ላይ የአዋሽን ወንዝ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ በማስቀየር የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመከላከል የሚከናወነው ሥራ አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግሥት የጎርፍ አደጋውን በዘላቂነት ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሠረቱ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት በተደረገ የጎርፍ መከላከል ቅድመ ዝግጀት ጎርፉን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የከሰም ግድብና መስኖ ጥገና ፕሮጀክት የሥራ ቡድን መሪ ደስታዓለም ተክለኃይማኖት፤ የአዋሽ ወንዝን አቅጣጫ ለማስቀየር የ5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የቆረጣ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል። 


 

ይህም የወንዙን አቅጣጫ በማስቀየር በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ ይደርስ የነበረውን የጎርፍ አደጋ መከላከል ያስችላል ነው ያሉት። 

ፕሮጀክቱ በሦስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸው፤ ለሥራው ውጤታማ አፈጻጸም የአካባቢው ማኅበረሰብ ያላሰለሰ ተሳትፎ እያደረገ ነው ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም