በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማክበር እየተደረገ ያለው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን ለማክበር እየተደረገ ያለው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ

ጎንደር ፤ ታህሣሥ 22 /2016(ኢዜአ) ፡- በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን በተለየ ድምቀት ለማክበር እየተደረገ ያለው ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ የማኔጅመንት አባላት የጎንደር ከተማን የጥምቀት በዓል ዝግጅትን በመቃኘት ጥምቀተ ባህሩ የሚከናወንበትን የአጼ ፋሲል የመዋኛ ስፍራ የፅዳት ስራን ዛሬ አስጀምረዋል፡፡
በዚህ ወቅት የቢሮው ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት የሚከበሩት የገናና የጥምቀት በዓላት ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መነቃቃት የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡
በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓልን በተለየ ድምቀት ለማክበር የተጀመረው ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠሉን መረዳት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡
ታቦታት በሚያርፉበት የአጼ ፋሲል መዋኛ ስፍራም እየተካሄደ የሚገኘው የጥገና ስራ ጥንታዊ ገጽታውን በጠበቀ መንገድ እየተካሄደ እንደሚገኝና ለበዓሉም ክፍት እንደሚደረግ መገንዘባቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዓሉን ለመታደም ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶች የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ ለማስቻልም የቅርሶች ጥገናና ክብካቤ ስራ በአጥጋቢ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስችላቸውን የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን እንደተመለከቱ ጠቅሰው፤ ከተማ አስተዳደሩ በተቀናጀ ሁኔታ እንግዶችን ለመቀበል ያደረገው ዝግጅት አጥጋቢ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በዓሉን ለመታደም የሚመጡ እንግዶች የትራንስፖርት እጥረት እንዳይገጥማቸው የበረራ ቁጥር ከፍ እንዲል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓት የሚከበረውን የዘንድሮ የጥምቀት በዓል እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ መቀጠሉን የገለጹት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው፡፡
ዐቢይና ንኡሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ስራ እየተገባደደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ስጋት ለማክበርም ህዝቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ የጥምቀት በዓል ብዛት ያላቸው የሀገር ውስጥ እንግዶች፣ ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ አምባሳደሮችና አርቲስቶች እንደሚታደሙ የሚጠበቅ መሆኑን ተመልክቷል፡፡
በጥምቀተ ባህሩ የጽዳት ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት የከተማው አመራር አባላትን ጨምሮ የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡