የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአዋጪ ልማት ፕሮጀክቶች በቂ ድጋፍ እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአዋጪ ልማት ፕሮጀክቶች በቂ ድጋፍ እያደረገ ነው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 22/ 2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአዋጪ ልማት ፕሮጀክቶች በቂ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጅግጅጋ ዲስትሪክት ለአዋጪ ልማት ፕሮጀክቶች በቂ የፋይናንስ ብድር እና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ዲስትሪክት ከሚደግፋቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ የተመረጡ ሰባት የልማት ፕሮጀክቶችን የመስክ ምልከታ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጅግጅጋ ዲስትሪክት እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ አንዲሆኑ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ጉብኝቱ አረጋግጧል።
የቋሚ ኮሚቴው ቡድን አስተባባሪ ዘውዱ ታደሰ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአራት ዓመታት በፊት ኪሲራ ውስጥ እንደነበረ ገለጸው፤ ከለውጡ ወዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤቶችን ካስገኙ ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
በአብነትም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የጅግጅጋ ዲስትሪክት የነበሩትን አራት ፕሮጀክቶች ወደ 49 ማሳደግ እንደተቻለ እና በዲስትሪክቱ ቅርንጫፎች ከ850 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ኮሚቴው በጥንካሬ ማንሳቱን ዶክተር ዘውዱ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዜሮ ተነስቶ እንደ ሀገር ሊታመኑ የማይችሉ ለውጦችን እያስመዘገበ የሚገኝ ትልቅ ተቋም እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ናቸው።
የጅግጅጋ ዲስትሪክት ደንበኞቹን በመደገፍ ዜጎች በማህበራዊና በኢኮኖሚ መለወጥ እንዲችሉ የበኩሉን ጥረት ማድረጉ አዎንታዊ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ፕሮጀክቶቹ ከኢንዱስትሪ ግብዓት እጥረት፣ ከኤሌክትሪክ ሀይል ማነስ እና የኮንትሮባንድ ንግድ በፕሮጀክቶቹ ምርት ላይ ከሚያደርሰው ተጽዕኖ አንጻር የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ትኩረት የሚሹ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኢንዱስትሪ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጌታሰው ፈንታው ከለውጡ ወዲህ የባንኩ አደረጃጀት እንደገና ተሰርቶ በቁርጠኝነት ወደ ስራ በመግባቱ የሚጠበቅበትን ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት እንዳስቻለው ተናግረዋል።
አዋጪ ለሆኑ የልማት ፕሮጀክቶች ተገቢውን የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ የሀገሪቱን ብልጽግና እውን እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጅግጅጋ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ወንዶሰን ተመስገን በቋሚ ኮሚቴው የተነሱ አስተያየቶች እንደ ግብዓት ተወስደው ስራ ላይ የሚውሉ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ዲስትሪክት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ከክልሉ መንግስት እና ከከተማ አስተዳዳሩ ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቶች በየዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር፣ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማስገኘት እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውን ከምክር በየቱ ማህበራዊ ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።