ቀጥታ፡

የከሰም ግድብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅሙ ዳግም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016(ኢዜአ)፦ የከሰም ግድብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅሙ ዳግም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በአፋር ክልል መካከለኛው አዋሽ የተከናወኑ የመስኖ ልማትና የተፋሰስ ሥራዎችን አስጎብኝቷል።

የከሰም ግድብ ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ግብዓት የሚውል የሸንኮራ አገዳ ለማምረት እና ለአፋር ቆላማ አካባቢዎች መስኖ ልማት ተብሎ የተገነባ ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ 500 ሚሊየን ሜትር ኪውቢክ ውሃ በመያዝ ለመስኖ ልማትና የጎርፍ አዳጋ ስጋትን ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመካከለኛው አዋሽ መስኖና ቆላማ አካባቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በቀለ በርገና እንዳሉት፤ የከሰም ግድብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅሙ ዳግም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።


 

በቀድሞው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ/ የተገነባው የከሰም ግድብ የውሃ ማስተንፈሻና መቆጣጠሪያ በር አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋት ደቅኖ ቆይቷል።

የከሰም ግድብ ግንባታው ተጠናቀቀ ተብሎ ሲመረቅ ብዙ የሲቪል ምህንድስና እና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ሳይጠናቀቁ መመረቁ የታለመለትን ዓላማ እንዳያሳካ አድርጎታል ብለዋል።

ግድቡ ሲገነባ 20 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ታስቦ የተሰራ ቢሆንም ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በመኖራቸው የሚፈለገውን ጥቅም ማግኘት አልተቻለም ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ግድቡ መያዝ ከሚገባው 500 ሚሊየን ሜትር ኪውቢክ ውሃ 380 ሚሊየን ብቻ መያዙን ገልጸው፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት ያስችላል ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በተለይም የውሃው መጠን መቆጣጠሪያ በር በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል የማኅበረሰቡን የጎርፍ ስጋት ማስወገድ ያስችሏል ብለዋል።

ያልተጠናቀቁ የግድቡ ግንባታ ሥራዎችን የማጠናቀቅ ሥራ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር በፍጥነት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በፕሮጀክቱ በዓመት 20 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት የሚያስችለው ሲሆን የመሠረተ-ልማት ግንባታ ሂደት በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል።


 

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ፤ እንደ ከሰምና መሰል ትልልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ልማት እንዲገቡ በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የከሰም ግድብ በአንድ በኩል የጎርፍ መጥለቅለቅን ለመከላከል በሌላ በኩል ደግሞ የመስኖ ልማት ለማከናወን ታልሞ የተገነባ ቢሆንም የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም በሰጠው ትኩረት የአስተዳደር፣ የፋይናንስና መሰል ችግሮቻቸው ተፈተው ወደ ሥራ መግባት የሚችሉበት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

የመካከለኛው አዋሽ የውሃ ኃብት፣ መልማት የሚችል ለም መሬት፣ የሰው ኃይል ፀጋን የታደለ መሆኑን ገልፀው፤ መንግሥት የዜጎች ኑሮን በማሻሻል የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር መሥራት ከተቻለ ተጨባጭ የፕሮጀክት አፈጻጸም ማስመዝገብ እንደሚቻል በሌሎች ሥራዎች አይተናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም