መገናኛ ብዙሃን የምርመራ ጋዜጠኝነትን በማጠናከር ለህዝብ ጥቅም መከበርና ብሔራዊ መግባባት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የምርመራ ጋዜጠኝነትን በማጠናከር ለህዝብ ጥቅም መከበርና ብሔራዊ መግባባት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን የምርመራ ጋዜጠኝነትን በማጠናከር ለህዝብ ጥቅም መከበርና ለብሔራዊ መግባባት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ መስጠት በማይፈልጉ ተቋማት ላይም የተጠያቂነት ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በመተባበር 'መረጃን ለህዝብ ጥቅም፣ በአገራዊ ኃላፊነት' በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁትና በውጤታማ መረጃ አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት እና የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዕውነቱ አለነ፣ የመረጃ አያያዝና አጠቃቅም ከህዝብ ጥቅምና ብሔራዊ መግባባት ሊቃኝ እና ቀይ መስመር ሊበጅለት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሁሉም በየራሱ ተናጠላዊ ፍላጎቶች ቢኖሩትም በመሰረታዊ የሀገር እና ህዝብ ጥቅም አኳያ ግን የመረጃ ተደራሽነት ከኃላፊነት ጋር አብሮ መናበብ እንዳለበት አንሰተዋል።
ለአብነትም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በታለመው ሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን እንዲሁም በጸረ ሙስና ትግል ዙሪያ ሚዲያዎች የጋራ ግብ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል መገናኛ ብዙሃን ከበጀት እና ስፖንሰርሽፕ ጋር ተያይዞ የሚገጥሟቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ የሚሰራ ትረስት ፈንድ ሊኖር እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ከምርመራ ዘገባዎች ጋር ተያይዞም የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር ችግሮችን ከማጋለጥ ባለፈ ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚያስችል አግባብ መዘገብ እንዳለበትም ገልጸዋል።
ለህዝብ ጥቅም መከበር ለሚሰሩ የምርመራ ጋዜጠኞችም አስተማማኝ የደህንነት ዋስትና ሊረጋገጥላችው እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የጋዜጠኞች ከተቋማት መረጃ የማግኘት መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ ገልጸው፤ በተጠየቁት ጉዳይ መረጃ መስጠት ፈቃደኛ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት አሰራር መስፈን እንዳለበትም አንስተዋል፡፡
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በዚሁ ጊዜ፣ ተቋሙ የመረጃ ነፃነት ህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት የተልዕኮው አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ እና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል እንዲሁም የህዝብን ጥያቄዎች ለመንግስት ተደራሽ የሚያደርጉ የሚዲያ ተቋማትን ለመገንባት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ መገናኛ ብዙሀን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የሙያ ስነ ምግባርን የሚያከብሩ፣ ሀገር የሚያፀና እና የተሟላና ወቅታዊ መረጃ የሚሰጥ ሚዲያ መገንባት እንደሚገባ አንስተዋል።
የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢዜአ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንዳሉት መረጃ እንደ ጦር መሳሪያ በመሆኑ በቅጡ ካልተያዘና ካልተመራ ሀገር እና ህዝብ ላይ አደጋ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን መረጃ ከቡድን ፍላጎት በላይ ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም መዋል እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው ፅሁፍ አቅራቢ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ እንዳሉት፤ የምርመራ ጋዜጠኝነት ለሀገር ደህንነት፣ ለልማት፣ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ትልቅ ሚና አለው።
የኢትዮጵያ ሚዲያ የምርመራ ዘገባዎች ውጤት ተኮር አለመሆን፣ የተደራጀ የምርምራ ቡድን አለመኖር፣ ለስራው ጉጉ አለመሆን፣ የደህንነት ጥበቃ አለመኖርና መሰል ድክመቶች እንዳሉባቸውም ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የጋዜጠኞች ክፍያ ማነስ፣ ምስጢረኝነት መስፋፋት፣ የምንጮች ፍርሀት፣ ዛቻና ማስፈራራት፣ የበጀት እጥረት፣ ራስን ለስራው አለመስጠትና ማበረታቻ አለመኖር እንደ ተግዳሮት ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የሚዲያ ፈንድ ማቋቋም፣ ለሚዲያ ተቋማት አስፈላጊ ሀብት መመደብ፣ የደህንነት ጥበቃ ማድረግ እና ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋራ ዕቅድና ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የሚዲያ ተቋማት ኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን ከህዝብ ጥቅም ጋር ማናበብ እንዳለባቸው እንዲሁ።