የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ እድገት ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ እድገት ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21 /2016 (ኢዜአ)፦ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ እድገት ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሌንሳ መኮንን ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በመዲናዋ በገበታ ለሸገር፤ በክልሎች ደግሞ በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ታሪክ ቀያሪ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ተከናውነው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በቅርቡም የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው በደቡብ ምዕራብ ክልል ኮንታ ዞን የሚገኘው የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅን ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ አካባቢውን ማራኪ ገጽታ አላብሶታል።
ፕሮጀክቱም ለቱሪስት መስህብ አስፈላጊ የሆኑ ሆቴሎች፣ ባህላዊና ዘመናዊ ሎጅ፣ ሬስቶራንትና የመዝናኛ ሥፍራዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የመሰረተ ልማቶች ተሟልተውለታል።
በገበታ ለሸገርና በገበታ ለሀገር ለአገልግሎት የበቁና እየበቁ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችም ለገጽታ ግንባታና ለየአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት አይነተኛ ፋይዳ እያበረከቱ ይገኛል።
በቀጣይም በተለያዩ ክልሎች በገበታ ለትውልድ የሚለሙ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ዘርፉን ይደግፋሉ ተብሎ ጠበቃል።
ከኢዜአ ቆይታ ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴዔታ ሌንሳ መኮንን፤ መንግሥት የቱሪዝም አቅሞችን በመለየት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።
በገበታ ለሀገር ለአገልግሎት የበቁና በሂደት ላይ የሚገኙ የመስህብ ልማት ሥራዎችም የመንግሥትን እይታ በማስፋት የቱሪዝም ኃብቶችን አልምቶ ለመጠቀም ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃሳብ አመንጪነት በተለያዩ የልማት ትልሞች ተቀርጸው ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች ተዳክሞ የነበረውን የኢትዮጵያ ቱሪዝም እንዲያንሰራራ እድል መፍጠሩንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ ያላቸውን ኃብት በማስተዋወቅና ጎብኚዎችን ለመሳብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ጎን ለጎንም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎውን እንዲያጠናክርና ፕሮጀክቶቹ በታለመላቸው ልክ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።