ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተመራጭ እየሆነ የመጣው እንጦጦ ፓርክ - ኢዜአ አማርኛ
ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተመራጭ እየሆነ የመጣው እንጦጦ ፓርክ

የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የእንጦጦ ፓርክ ከመዝናኛ ባለፈ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተመራጭ ስፍራ ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ፍሰት ከማሻሻል ባሻገር ገጽታዋን ከቀየሩ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው እንጦጦ ፓርክ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ ለአገልገሎት ክፍት መሆኑ ይታወሳል፡፡
ፓርኩ የስፖርት ማዕከላት፣ ቤተ-መጻሕፍት፣ መዝናኛዎች፣ የስነ-ጥበብ ጋለሪ፣ አምፊ ትያትር፣ የፈረስ መጋለቢያ ስፍራ፣ ምግብ ቤቶችና የቡና ሱቆች ፣ሰው ሰራሽ ሐይቅ እና ለጎብኚዎች ተለይተው የተዘጋጁ የመጓዣ መንገዶችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በውስጡ ያካተተ ድንቅ የመዝናኛ ስፍራ ነው፡፡
ለመዲናዋ የቱሪስት መስህብ የሆነው ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን የአገልግሎት ዘርፍ ኢኮኖሚ ከማሳደግና የከተማይቱን ገጽታ ከመቀየር አኳያ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በግልና በቡድን በመሆን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚያዘወትሩበት ስፍራ ሆኗል።
በፓርኩ ስፓርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ያገኘናቸው አቶ መስፍን ኃይሉ እንደሚሉት፤ ከሁለት ዓመት በፊት ከሕክምና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ምክረ ሃሳብ መሰረት በማድረግ በእንጦጦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት መጀመራቸውን ይገልጻሉ።
ፓርኩ በርካታ ስፖርተኞችና ቱሪስቶች በተለይ በእረፍት ቀናት የሚዝናኑበት ተስማሚ ስፍራ መሆኑን ገልጸው፤ ፓርኩ የሚያስፈልገው መሰረተ ልማት የተሟላለት በመሆኑ በበርካታ ሰዎች ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ፓርኩ በመምጣት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁና ተፈጥሮን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
ተማሪ ሃና ኡርዛ በበኩሏ ከትምህርቷ ጎን ለጎን ስፖርት ለመስራት የእንጦጦ ፓርክ ምርጫዋ እንደምታደርግ ገልጻለች።
የፓርኩ መገንባት በተለይ ወጣቶች በአካልና ስነ ልቦና ራሳቸውን እንዲያጎለብቱ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ዘነበ ግርማ እና አቶ ከበደ ምንዳ፤ በተፈጥሮ የታደለውና የመዝናኛ ስፍራዎች አሟልቶ የያዘው የእንጦጦ ፓርክ የመዲናዋ ተመራጭ የመዝናኛ ስፍራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወጣቶች በአልባሌ ስፍራዎች ከመዋል በፓርኩ ስፖርታዊ እንቅሰቃሴዎችን በማድረግ ጤንነታቸውን መጠበቅ እንደሚችሉም ገልጸዋል።