መገናኛ ብዙሃን የሀገርና ሕዝብ ጥቅምን ባስቀደመ መልኩ መረጃን በኃላፊነት ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የሀገርና ሕዝብ ጥቅምን ባስቀደመ መልኩ መረጃን በኃላፊነት ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙሃን የሀገርና ሕዝብ ጥቅምን ባስቀደመ መልኩ መረጃን በኃላፊነት ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም እና ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በመተባበር ``መረጃን ለህዝብ ጥቅም፣ በአገራዊ ኃላፊነት`` በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁትና በውጤታማ መረጃ አስተዳደርና አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣ የዲሞክራሲ ተቋማት እና የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት ህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ግንዛቤ መፍጠር ከተቋማቸው ተልዕኮዎች መካከል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የመረጃ ነፃነት እንዲረጋገጥ የሕግ ማዕቀፍ ከማሻሻል ባሻገር መገናኛ ብዙሀን እና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
ሚዲያ ለህዝብ ጥቅም መወገን እንዳለበት ጠቅሰው፤ የሕግ የበላይነት እንዲኖር የሚሰራ፣ ሙስናን ና ብልሹ አሰራሮችን የሚያጋልጥ፣ የህዝብን ጥያቄዎች ለመንግስት ተደራሽ የሚያደርጉ የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማዳበር ይገባል ነው ያሉት፡፡
እውነተኛ መረጃን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በህዝብና መንግስት መካከል አመኔታ መፍጠር እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በዚሁ ጊዜ፤ መገናኛ ብዙሀን አሉታዊ ችግሮችን በመንቀስ ለህዝብ ጥቅሞች መከበር ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህም ጠንካራና ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር መንግስት እንዲኖር ያግዛል ነው ያሉት።
በመሆኑም የሙያ ስነ ምግባርን የሚያከብር፣ ሀገር የሚያፀና እና የተሟላና ወቅታዊ መረጃ የሚሰጥ ሚዲያ መገንባት እንደሚገባ አንስተዋል።
የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ለዚህ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠር የሕግ ማዕቀፍ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዕውነቱ አለነ በበኩላቸው መረጃን ለህዝብ ጥቅም ተደራሽ ማድረግ ለብሔራዊ ጥቅምና ብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሚዲያዎች መረጃ መስጠት፣ መቀበልና ማስተላለፍ ከኃላፊነት ጋር አብሮ መናበብ እንዳለበት ገልፀው፤ እንደ ሀገር በመረጃ አሰጣጥ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ በኃላፊነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ሲባል ሚዲያ በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግብ ይዘው በኃላፊነት መስራት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ኢዜአ የሕዝብ ጥቅምን መሰረት ያደረጉ የመረጃ ተደራሽነት ላይ የተለያዩ መድረኮች ሲያካሂድ መቆየቱን አንስተዋል።
መድረኩ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የሕዝብና ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረጉ መሰል ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡