ቀጥታ፡

ወጣቶች የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን በንቃት ሊዋጉ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ)፦ወጣቶች ሰላም የሰፈነባት ሀገርን ለመረከብ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃዎችን በንቃት እንዲታገሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ አሳሰቡ።

በጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት መከላከያ መንገዶች ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚኒ ሚዲያ አባላት ተማሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል።


 

ዋና ዳይሬክተሩ በስልጠናው ላይ እንደገለጹት የቴክኖሎጂ እድገት ለመማር ማስተማር ሂደት መቀላጠፍ ጉልህ አስተዋፅኦ ቢኖረውም ለስነ-ልቦና ጫና እና ለውጤት ማሽቆልቆል ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ከዚህ አኳያ ተማሪዎች እጃቸው ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ በአግበቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው ተማሪዎች የሚዲያና የመረጃ አጠቃቀም ክህሎታቸውን በማሳደግ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መዘጋጀቱን ገልጸው ተሳታፊ ተማሪዎችም ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ለሌሎች ማካፍል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ሰልጣኝ ተማሪዎች በበኩላቸው ስልጠናው የሚዲያና የመረጃ አጠቃቀም ክህሎታቸውን በማሳደግ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላቸው መግለጻቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በስልጠናው በአዲስ አበባ ከተማ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ 32 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 96 የሚኒ ሚዲያ አባላት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም