ኢትዮጵያ ለቱሪዝም መሰረተ ልማት የሰጠችው ትኩረት ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስና ኃብት የማኖር ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለቱሪዝም መሰረተ ልማት የሰጠችው ትኩረት ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስና ኃብት የማኖር ማሳያ ነው
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 20 / 2016(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለቱሪዝም መሰረተ ልማት የሰጠችው ትኩረት ጎብኚዎችን ከመሳብ ባለፈ ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስና ኃብት የማኖር ማሳያ ነው ሲል የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማሕበር ገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሀሳብ አመንጪነት እየተገነቡ ያሉ የገበታ ለሸገርና የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውጤታማ የቱሪዝም የልማት ሥራዎች እየሆኑ መጥተዋል።
ከነዚህም ውስጥ በገበታ ለሸገር ከተገነቡና ለአገልግሎት ከበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የእንጦጦ፣ የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች ይጠቀሳሉ።
በገበታ ለሀገር ደግሞ በቅርቡ የተመረቁትን የኮይሻ ፕሮጀክት አካል የሆኑትን ሀላላ ኬላና የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅ ጨምሮ የጎርጎራ እና የወንጪ-ደንዲ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚሁ መስህቦች ጎብኝዎችን ወደ አገሪቱ ለማምጣት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥሩም ነው የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማሕበር የሚገልፀው።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ፍጹም ገዛኸኝ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በገበታ ለሀገርና በገበታ ለሸገር ተግባራዊ የተደረጉት ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
እነዚሁ ፕሮጀክቶችም የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ አስጎብኚዎች ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ለመሥራት የሚያስችል ዕድል ተከፍቶልናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ቢኖሩም በበቂ ሁኔታ አልምቶ ከመጠቀም አንጻር ክፍተቶች ሲታዩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
የገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የመስህብ መዳረሻነት ክፍ የሚያደርጉ እና ከቱሪዝም ልማት አንጻር ያለውን እምቅ ሀብት አልምቶ ለመጠቀም የዕይታ ለውጥ ያመጡ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
ለአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉ ቅርስና ሀብት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተሻጋሪ ጥቅም እንዲሰጡ በአግባቡ ሊጠበቁ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት በዚህ ከቀጠሉ በጥቂት ጊዜ ኢትዮጵያ በዓለም ካሉ ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደምትሰለፍ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የካራቫን ቱር ኤንድ ትራቭል ኤጀንሲ ባለቤት አቶ አሚን ያሲን በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ለቱሪዝም ዘርፍ እየተሰጠ ያለው ትኩረት የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት የተገነቡት የቱሪስት መስህቦች የዘርፉን እድገት ለማፋጠን የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖራቸውም እንዲሁ።
በገበታ ለሀገር የተሰሩ ፕሮጀክቶች ዘመናዊነትን የተላበሱ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ መሆናቸውን ገልጸው ለቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ አማራጮችን ያጎናጸፉ ናቸው ብለዋል።
እንደ አቶ አሚን ገለፃ፤ ፕሮጀክቶቹ የተሟላ እና ምቹ መሰረተ ልማት ያላቸው ከገንዘብ፣ ከጊዜና ከሌሎች አስፈላጊ ግብአት አንፃርም የጎብኝዎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።