የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚረዱ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚረዱ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ

ሆሳዕና፤ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማጠናከር የሚረዱ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ እንደሚገባ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ ገለጹ።
የሀላባ ብሄር የዘመን መለወጫ የሆነው ሴራ ወይም መንገሳ በዓል "ሴራችን የአንድነታችን ማሳያ ድንቅ ምልክታችን ነው" በሚል መሪ ቃል በሆሳዕና ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
'ሴራ' ማለት በሃላባ ቋንቋ መተዳደሪያ ደንብ ማለት ሲሆን፣ በብሄረሰቡ ዘንድ በየዓ
መቱ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል 'ሴራ' ወይም መንገሳ ተብሎ ይጠራል።
በመድረኩ ላይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑሪዬ እንደተናገሩት በክልሉ በርካታ የሆኑ ሰላምንና ትስስርን የሚያጠናክሩ እሴቶች አሉ።
እነዚህ እሴቶች ሳይበረዙ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
ባህላዊ እሴቶቹ የፍትህ ስርዓትን በማገዝ ረገድ ለግጭት አፈታት እንዲሁም ሰላምን ለማረጋገጥ የሚረዱ እንዲሁም መደጋገፍና አብሮነትን የሚያጸኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሃላባ ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው 'ሴራ' ሲሆን በዓሉ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መተዳደሪያዎችና የቀን መቁጠሪያዎች ጭምር ያካተተ መሆኑን አንስተው፣ ይህንኑ በጎ እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አንስተዋል።
የክልሉ ምክር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ መነቴ ሙንዲኖ በበኩላቸው የዘመን መለወጫ በዓሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች በሰከነ መንገድ የሚፈቱበት የሰላምና አብሮነት እንዲሁም የቀጣይ ተስፋ የሚሰነቅበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓሉ ለሰላምና አብሮነት መጠናከር እንዲሁም ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ናቸው።
''ነባር እሴቶች አብሮነትንና አንድነትን የሚሰብኩ ናቸው'' ያሉት አቶ አብርሃም፣ ለተጀመረው የጋራ ትርክት ግንባታ ተጨማሪ አቅም የሚሆኑ ናቸውም ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወጣት ሲና ኃይለ ማርያም በበኩሏ ''ኢትዮጵያ አስደማሚ የሆኑ አኩሪ ባህል፣ ታሪክና እሴቶች ያላት ሀገር ናት'' ብላለች።
''ባህሎቻችንን በመጠበቅና በመንከባከብ እንዲሁም በጽሁፍ ተሰንደው ለዓለም እንዲተዋወቁና እንዲተላለፉ ሁሉም ሀላፊነቱን መወጣት አለበት'' ብላለች።
በሆሳዕና የባህል አዳራሽ በፓናል ውይይት በተከበረው በዓል ላይ ባህላዊ አልባሳትና ሌሎች ባህሉን የሚገልጹ ትዕይንቶች ለታዳሚያን ቀርበዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ፣ የሀላባና የሀድያ ዞን አመራሮች እንዲሁም ከክልሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተሳትፈዋል።
በዓሉ ጥር 4 እና 5 ቀን 2016 ዓ.ም በሃላባ ዞን ደረጃ በሲምፖዚየምና በሌሎች መርሐ ግብሮች በቁሊቶ ከተማ እንደሚከበርም ተገልጿል።