በሀገራዊ ምክክሩ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር የኪነጥበብ ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር የኪነጥበብ ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክሩ የዜጎች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር የኪነጥበብ ባለሙያዎች ግንዛቤ የሚያስጨብጡ የኪነጥበብ ስራዎችን እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጥሪ አቀረቡ።
"ለሀገራዊ ምክክር እና ሀገራዊ መግባባት የኪነ-ጥበብ፣ የማስታወቂያ እና የሁነት ዝግጅት ተቋማትና ባለሙያዎች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ስለ ሀገራዊ ምክክር ምንነትና አስፈላጊነት፣ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ዐበይት ተግባራት ለተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለስኬቱም ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማጎልበት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማት ተሳትፎም ሊጨመርበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዚህ አኳያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ስለ ምክክሩ ሳቢ፣ ግልፅና አዝናኝ በሆነ መንገድ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ አቅም ስላላቸው ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ ስር የሰደዱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሚናው የላቀ በመሆኑ ለስኬታማነቱ በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የማስታወቂያና የኪነጥበብ ባለሙያው አርቲስት ተስፋዬ ማሞ ሁለንተናዊ ሰላም የሰፈነባትና የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ሃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።
ሀገራዊ ምክክሩ በተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ኪነጥበብን ተጠቅሞ ህዝቡን ማስገንዘብ እንደሚገባ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበራት ዘርፍ ፕሬዚዳንት ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ በበኩሉ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የኪነጥበብ ስራዎችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የቆዩ ውስብስብ ችግሮችን ፈትቶ ወደተሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገር ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ እየተደረገ ያለውን ዝግጅትም አድንቋል።
በመሆኑም ለምክክሩ መሳካት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከኮሚሽኑ ጋር በቅርበት የመስራት ሀገራዊ ሃላፊነት አለብን ብሏል።