ቀጥታ፡

የአፍሪካ ሮቦቲክስ ውድድር በመጪው የካቲት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):-  የአፍሪካ ሮቦቲክስ ውድድር በመጪው የካቲት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የትምህርትና ውድድር ማዕከል አስታወቀ።

የኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ በቻይና ውዥን 2023 ዓለም አቀፍ የትምህርት ሮቦቲክስ ፌስቲቫል ላይ በተካሄደው ውድድር ከ27 አገራት ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ኢትዮጵያን ላስጠሩ 21 ታዳጊዎች የሽልማትና የምሥጋና መርሐ ግብር ዛሬ አካሂዷል። 


 

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰናክሬም መኮንን በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የኢትዮጵያ የታዳጊዎች ቡድን በቻይና ውዥን በተካሄደው የሮቦቲክስ ውድድር ሦስት ዋንጫዎችን አሸንፏል።

ውድድሩ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በቴክኖሎጂው ዘርፍ የሀገራቸውን ስም ከፍ እንደሚያደርጉ ያሳዩበት ነው ብለዋል።

ታዳጊዎቹ ምርጥ ዲዛይነሮች፣ ኢንጂነሮችና ፕሮግራመር እንዲሆኑ ሥልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ጠቅሰው በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተጨባጭ ውጤት እንደሚያመጡም ተስፋ አለን ነው ያሉት።

አቶ ሰናክሬም አክለውም የአፍሪካ ሮቦቲክስ ውድድር በመጪው የካቲት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ በውድድሩ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ታዳጊዎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ታዳጊዎች የራሳቸውን የዲዛይን፣ የኢንጂነሪንግና የፕሮግራሚንግ ክህሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

በዚህም ውጤት በማምጣት አገራቸውን እንደሚያኮሩ ነው የገለጹት።

በሽልማት መርሐ ግብሩ የተገኙት የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ከድህነት ለማላቀቅ ታዳጊዎችን በቴክኖሎጂ ማብቃት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የነገ የኢትዮጵያ ብሎም የዓለም ተስፋ የሚሆኑ ታዳጊዎች ላይ የጀመረው ስራ የሚያስመሰግንና ተጠናክሮ መጠቀል ያለበት ነው ብለዋል።

በቻይና በነበረው ውድድር ላይ የተሳተፉ ታዳጊዎች በውድድሩ በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚቻል ልምድ ስለመቅሰማቸው ሀሳባቸውን አካፍለዋል።  

ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ ከ14 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሮቦቲክስ ትምህርትና ውድድር ማዕከል ሆኖ መመስረቱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በተለያዩ ሀገራት በሚካሄዱ ዓለምአቀፍ የሮቦቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ እያደረገም ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም