ቀጥታ፡

አብሮነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ አብሮነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ  ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ታህሳስ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ  ሊካሄድ ነው።

መድረኩ የሚካሄደው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአብሮነት ቀን አስመልክቶ እንደሆነ አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴው ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

ቀኑን የአብሮነት ሳምንት በሚል በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅት ማጠናቀቁንም ጠቅሷል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ፤ ቀኑ "ብዝኃነትን መኖር" በሚል መሪ ቃል አብሮነትን በሚያጎላ መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር አብራርተዋል።

በዚህም መሰረት ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም አብሮነትን በተግባር በሚል የተቸገሩትን በመርዳትና ሌሎች በጎ ተግባራትን በማከናወን ይከበራል።

ታኅሣሥ 23 ቀን አብሮነትን በሚዲያ በሚል ሕብረተሰቡ በተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴዎች ስለአብሮነት እንዲነጋገር እና ሀሳብ እንዲለዋወጥ የሚያስችል መርሐ ግብር መኖሩን ጠቁመዋል።

ታኅሣሥ 24 ስፖርትና አብሮነት በሚል ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የማስ ስፖርት ይካሄዳል።

የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ አምባሳደሮች እና የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ  ታኅሣሥ 25 ቀን በሳይንስ ሙዚየም እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ተቋማት የተውጣጣው አስተባባሪ ኮሚቴ፤ ለሁነቶቹ መሳካት በቂ ዝግጅት ማድረጉ ተነግሯል።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ  ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብዝኃነትን ለማስረጽና አብሮነትን ለማጠናከር በቀጣይነት እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ አቶ ተስፋዬ ውብእሸት በበኩላቸው ቤተ እምነቶች አብሮነትን መስበክ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ቢሆንም በወጣው መርሃ ግብር በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።


 

 ታህሳስ 25 በሚካሄደው መድረክ የዳበረ የፖለቲካ ባህል፣ ሰላምና አብሮነት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል።

በመሆኑም በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአካልና በበየነ መረብ እንዲሳተፉ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም