መጪውን የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ እንቁላል፣ ዶሮና የወተት ተዋፅዖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
መጪውን የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ እንቁላል፣ ዶሮና የወተት ተዋፅዖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- መጪውን የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ እንቁላል፣ ዶሮና የወተት ተዋፅዖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የወተት፣ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የማር፣ የዓሣ እና የሥጋ ምርቶችን ለማሻሻል ሀገራዊ የመንግሥት ፕሮግራም ሆኖ እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት በዕቅዱ መሠረት ጥሩ ውጤት እየመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በያዝነው ዓመትም የበለጠ ለማሳካት የሁላችንም ያላሰለሰ ጥረት ልናደርግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባም በሌማት ትሩፋት ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል።
ከንቲባዋ የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ገበያን በማረጋጋትም ጭምር አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም ባለፉት በዓላት እንቁላልና ዶሮን ጨምሮ የወተት ተዋፅዖ በስፋት ለገበያ እንዲቀርብ መደረጉን ተናግረዋል።
አሁን ላይ በቀን 1 ሚሊየን እንቁላል ለገበያ ማቅረብ የተቻለበት አቅም በሌማት ትሩፋት ተፈጥሯል ብለዋል
ኢዜአ በለሚ ኩራና በየካ ክፍለ ከተሞች በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በእንስሳትና ዶሮ እርባታ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎችን አነጋግሯል።
ተጠቃሚዎቹ እንደገለጹት፤ ሥራቸው የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ኑሯቸውን ማሻሻል ችለዋል።
በወተት እና በእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ የተሰማሩት አቶ ዮናስ በድሉ፤ ከወተት፣ ከዶሮና እንቁላል ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ የቤተሰባቸውን ኑሮ መቀየር መቻላቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር በማስታወስ፤ ዛሬ ላይ ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ምርቶቻቸውን ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጋቸውን አብራርተዋል።
የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚው ሐሰን በሽር በበኩሉ፤ ለበዓል የሚሆን ወተትና የወተት ተዋፅዖን ጨምሮ እንቁላል እና ዶሮዎችን ለገበያ እያዘጋጀን እንገኛለን ብሏል።
ሌላው ተጠቃሚ አቶ አለሙ አርጋው፤ ሰዎች እራሳቸውን ከጠባቂነት በማላቀቅ በተሰማሩበት ዘርፍ በትጋት ከሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ እኔ ማሳያ ነኝ ይላሉ።
እሳቸውም ለገና በዓል የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህ በዶሮም ሆነ በወተት ላም እርባታ የተሰማሩ አካላት የሌማት ትሩፋት እያስገኘላቸው ካለው ተጠቃሚነት አኳያ ሥራቸውን የበለጠ ለማስፋት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የማምረቻ ቦታ እና የውሃ እጥረት እያጋጠማቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ዮናስ በድሉ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ሥራቸውን ሊያስተጓጉልባቸው እንደሚችል አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ያለውን ችግር በመረዳት አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል ነው ያሉት።
አቶ አለሙ አርጋው በበኩላቸው፤ በቦታ ጥበት ምክንያት ችግሮች እየገጠማቸው እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተሰማሩበት የዶሮና የወተት ላሞች እርባታ በቂ ቦታ የሚሻ በመሆኑ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባዩ ሽጉጤ፤ ችግሮቹን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ከመሥሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ችግሮች ከግንባታ ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ከውሃ ጋር በተያያዘ ለሚነሳው ችግርም የጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮና በቤት ውስጥ ለተለያየ ነገር ጥቅም ላይ የሚውልን ውሃ መልሶ በማጣራት መጠቀም እንዲችሉ የማስተማርና የማገዝ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።