ለስፔስ ሳይንስ እውቀትና ልማት ዘርፍ ውጤታማነት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ይወጣል--የተቋሙ ፕሬዚዳንት - ኢዜአ አማርኛ
ለስፔስ ሳይንስ እውቀትና ልማት ዘርፍ ውጤታማነት የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ይወጣል--የተቋሙ ፕሬዚዳንት
ጋምቤላ ፤ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ):- የስፔስ ሳይንስ እውቀትና ልማት ለአገር እድገትና ዘመናዊነት ሚናው የጎላ በመሆኑ ለዘርፉ ውጤታማነት ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን እንደሚወጣ የጋምቤላ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዲሪባ ኢቲቻ አስታወቁ።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ብሔራዊ የስፔስ እና ዓለም አቀፍ የጂ.አይ.ኤስ ቀንን ዛሬ አክብሯል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ዘርፍ ልማት እንደአገር ዘመናዊ የዲጅታል ኢኮኖሚና ሁለንተናዊ እድገት እንዲረጋገጥ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።
በመሆኑም መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ደረጃውን የጠበቀ ብሔራዊ የስፔስ ሳይንስ ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም ማድረጉን ገልጸዋል።
የስፔስ ሳይንስ እውቀትና ልማት ለአንድ አገር እድገትና ዘመናዊነት የጎላ ድርሻ ስለሚኖረው ለዘርፉ ውጤታማነት ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂ.አይ.ኤስ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ በላቸው ፀሐዬ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ምርምሮች ሲደረጉ ቆይተዋል።
በዚህም ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎች ወደዘርፉ በማምጣት የአገሪቱን የስፔስ ሳይንስ ማሳደግ እንዲችሉና የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እውን እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከሁሉም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀራረብ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳለጥ የጀመረው ጥረት ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቀኑ ሲከበር በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲና በስፔስ ሰይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት መካከል በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ፊርማ ስነ-ስርዓትም ተከናውኗል።
የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማ በዩኒቨርሲቲው ልዩ ተሰጥኦ ያለቸውን ተማሪዎች ማብቃት፣ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎችን ማማከር፣ ምርምሮችን በጋራ ማካሄድና በዘርፉ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተመልክቷል።