ቀጥታ፡

በደም እጦት ምክንያት ዜጎች ለከፋ ጉዳት እንዳይዳረጉ ሁሉም ሰው በበጎ ፈቃደኝነት ደም ሊለግስ ይገባል -- የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ አገልግሎት

አዳማ ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ)፦ በደም እጦት ምክንያት ዜጎች ለከፋ  ጉዳት እንዳይዳረጉ የሃይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የተለያዩ አደረጃጀቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

አገልግሎቱ ደም ለጋሽ በጎ ፍቃደኞች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ክበቦችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ በአዳማ አካሄዷል።

በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ደምና ህብረህዋስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደገለፁት አገልግሎቱ በጎ ፈቃደኞች በስፋት ደም እንዲለግሱ ለማስቻል የተለያዩ ስራዎች እየሰራ ነው።

ባለፉት አምስት ወራት ከ139 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን ገልጸው የሆስፒታሎችና በየደረጃው የሚገኙ ጤና ተቋማት የደም ፍላጎት ከማሟላት አንፃር ብዙ ይቀራል ብለዋል።

ዘንድሮ 427 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ እቅዱን ለማሳካት የሃይማኖት ተቋማት፣ የትምህርት ተቋማት፣ የተለያዩ አደረጃጀቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች፣ ሃይማኖት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

ደም የሚፈልጉ እናቶች፣ ህፃናትና በትራፊክ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ህይወት ለመታደግ ሁሉም በበጎ ፈቃደኝነት ደም መለገስን ባህል ማድረግ አለበት ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አብረሃም ታደለ 32 ጊዜ ደም በመለገስ በተለያዩ የዜጎችን ህይወት መታደግ መቻላቸውን ይናገራሉ።


 

ደም መለገስ ምንም ጉዳት እንደሌለው የሚናገሩት አቶ አብረሃም ሁሉም ሰው በዚህ በጎ ስራ መሳተፍ እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ዳዊት ተስፋዬ ለተከታታይ 32 ዓመታት 96 ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።

ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበር ደም እየለገሱ መሆኑን ጠቅሰው ባለቤታቸውና ሶስት ልጆቻቸው በየጊዜው ደም እየለገሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ ደም ባንኮችም ካለው የደም ፍላጎት አንጻር ህዝቡ ደም መለገስን እንዲያጠናክር መጠየቃቸውን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም