በገበታ ለትውልድ የሚለማው ሎጎ ሐይቅ ቀጣናውን የቱሪስት መደራሻ ለማድረግ ያስችላል - የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ - ኢዜአ አማርኛ
በገበታ ለትውልድ የሚለማው ሎጎ ሐይቅ ቀጣናውን የቱሪስት መደራሻ ለማድረግ ያስችላል - የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

ደሴ፤ ታህሳስ 20/2016(ኢዜአ)፦ "በገበታ ለትውልድ የሚለማው የሎጎ ሐይቅ ከደሴ ከተማ ፈጣን መስተንግዶ ጋር ተዳምሮ ቀጣናውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ነው" ሲሉ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ገለፁ፡፡
የደቡብ ወሎ ዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራር አባላት በሐይቅ ከተማ በገበታ ለትውልድ የሚለማውን ሎጎ ሐይቅ የዝግጅት ሥራ ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ለቱሪስት መዳራሻ የሚሆኑ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቦታዎች በስፋት ይገኛሉ።
ሆኖም ያሉ ጸጋዎችን በአግባቡ በማጥናትና በመለየት፣ ወደ ልማት እንዲገቡ በማድረግና በማስተዋወቅ በኩል ውስንነት እንደነበር አውስተው፤ በዚህም ከቱሪዝም ዘርፉ መገኘት ያለበትን ጥቅም ያህል ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በገበታ ለትውልድ መርሃ ግብር የሎጎ ሐይቅና አካባቢውን በማልማት ለቱሪስት መስህብ ለማዋል የተደረገው እንቅስቃሴ ለዘርፉ እድገት ታላቅ አሻራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በዞኑ ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በጥናት በመለየትና በማልማት የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና ለዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሎጎ ሃይቅ ፕሮጀክት ዲዛይን ተጠናቆ የዝግጅት ሥራ መጀመሩን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ "ተገቢውን ክትትል ለማድረግ የሚያስችል ከዞኑ፣ ከሐይቅ ከተማና ተሁለደሬ ወረዳ የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል" ብለዋል።
የአርሶ አደሮች የካሳ ክፍያ እንዲፈጸም ክልሉ ውሳኔ ላይ በመድረስ መጽደቁንና ሌሎች ተግባራት ጎን ለጎን እየሄዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ "ከአካባቢው ተነሽ አርሶ አደሮች ጋርም መግባባት ላይ ተደርሷል" ብለዋል።
በዚህም "ከአካባቢያቸው የሚነሱ አርሶ አደሮችን መልሶ ለማቋቋምም እየተሰራ ነው" ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ህብረተሰቡ ሰላሙንና አንድነቱን በመጠበቅ ለፕሮጀክቱ ፍጻሜ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ነኢማ እሸቱ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ የከተማውን ሁለተናዊ እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ መደገፍና ማገዝ ይጠበቅበታል።
ፕሮጀክቱ ከደብረ ብርሃን እስከ ግሸን ደብረ ከብሬ፣ ውጫሌና ላሊበላን በማስተሳሰር ሰፊ የቱሪስት ቀጣና በመፍጠር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት አመቺ ቦታ ላይ ያለ በመሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ከካሳ አከፋፍል ጋር ተያይዞ ቅሬታ እንዳይፈጠርና የዝግጅት ሥራው እንዳይስተጓጎል ከአርሶ አደሩ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን ጠቁመው፤ የልማቱ አጋዥ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አብራርተዋል፡፡
"የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ወደ ከተማችን መምጣቱ እድለኛ ነን"ያሉት ምክትል ከንቲባዋ፤ የአካባቢው ማህበረሰብና ወጣቱ ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆንም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።